መደራጀት ሃይል ነው፣ የመደራጀት ዋና ግቡ በተናጠልና በተበታተነ መንገድ ማሳካት የማንችለውን በህብረት በቀላሉ ከግብ ማድረስ ማስቻሉ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስገነዘቡ።
ወጣቶች ተደራጅታችሁ መንቀሳቀሳችሁ ለተጠቃሚነታችሁ እና በሁሉም ዘርፍ ያላችሁን ተሳትፎ ለማጐልበት ወሳኝ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ናት በማለትም አክለዋል፡፡
የምንሰራው ከምንም በላይ ለወጣቶች እና ለነገ ትውልድ ተጠቃሚነት ነውም ብለዋል።
የከተማችን አመራሮች 70 በመቶ ያህሉ ወጣቶች ናቸው ያሉት ከንቲባዋ፣ የወጣቶችን ስብዕና መገንቢያ እና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በስፋት እየሰራን ያለነዉም በአካል እና ስነልቦና የጎለበታችሁ ብቁ ዜጋ ትሆኑ ዘንድ ነዉ በማለት ገልጸዋል።
የከተማችን ወጣቶች በልማት ላይ ያላችሁ ተሳትፎ በተለይ በበጎ አድራጎት ስራ ያከናወናችሁት ስራ እጅግ ያስመሰግናችኋልና በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁም ብለዋል።