የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ማለዳ በ11 ክፍለ ከተሞች ከ5 ቢለየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው የተገነቡ 1 ሺህ 277 ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸውን ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በዛሬው እለት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች 122 የስፖርት ማዘውተሪያ እና 1 ሺህ 155 የህፃናት መጫወቻ ማዕከላት በጥቅሉ 1 ሺህ 277 መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ይህ ውሳኔያችን በአዕምሮና በአካል የዳበረ ትውልድ ለመገንባት ከከተማችን ሀብት መሬት እና በጀት፣ ከእኛ ከአመራሮች እና ከሰራተኛው ደግሞ ጉልበት እና ጊዜ እፍታውን ወስደን እንዲሁም ማህበረሰቡን በማስተባበር ለትውልዱ ቅድሚያ ስጥተን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ገንብተናል ብለዋል።
ባለፋት 3 ዓመታት ለስራ ቦታዎች እና ለመኖሪያ አካባቢዎች ጭምር ትኩረት በመስጠት በድምሩ 3 ሺህ 789 የህፃናት የመጫወቻ ማዕከላትን እና 1ሺህ 530 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ገንብተን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል በማለትም ገልጸዋል።
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ እነዚህ ደረጃዉን ጠብቀን የገነባናቸዉ መሰረተ ልማቶች 50 በመቶ ወጪያቸው የተሸፈነዉ በማህበረሰቡ መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል ሲሉም ነው ያከሉት።
ለወጣቶችና ህጻናት የስፖርት ማዘውተሪያና መጫወቻ ማዕከላትን ለመገንባት ሲደረግ በነበረው ጥረት ሁሉ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱና ላስተባበሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።