AMN- ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም
የዋሽንግተን ዋነኛ አጋር የሆኑት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያን የሚያካትተው ማስጠንቀቂያው ሀገራቱ ከአሜሪካ አንጻር በውል የታሰረ ስምምነት ላይ ካልደረሱ በቀር ርምጃ አይቀሬ መሆኑን ዋይት ሃውስ አስታውቋል፡፡
47ኛው የአሜሪካ ርእሰ ብሄር ከበርቴው ዶናልድ ትራምፕ ለ90 ቀናት የሰጡት የንግድ ድርድርና የስምምነት ቀነ ገደብ ነገ ይጠናቀቃል፡፡
በኒዘሁ 3 ወራት ውስጥ ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ የንግድ ሽርክና ያላቸው ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት አሸናፊም ተሸናፊም በሌለበት አውድ ጤናማ የንግድ ልውውጥ መከወን ይችሉ ዘንድ ሀገራት ከዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር መስማማት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
በርካታ ሀገራት የትብብርና የስምምነት ፍላጎት አሳይተዋል ባዩ የነጩ ቤተመንግስት በአንጻሩ ለድርድር ለዘብተኛ ሆነዋል ያላቸው ሀገራትን በስም ጠቅሶ የንግድ እቀባ ለመጣልም ዝቷል፡፡
በተሰጡት 90 ቀናት ውስጥ ረብ ያለው ርምጃ ባለመውሰድ የንግድ ታሪፍ ጭማሪ የሚጣልባቸው ተብለው 14 ሀገራት ሰፍረዋል፡፡ እነዚሁ ሃገራት ከ25 እስከ 40 በመቶ የሚደርስ የውጭ ንግድ ታሪፍ እንዲጣልባቸው ረቂቅ ውሳኔ ቀርቧል፡፡
በእስያ አህጉር ዋነኛ የአሜሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ሸሪኮቹ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የንግድ እቀባ ገፈቱ ሊደርሳቸው ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡
እያንዳንዳቸው የ25 በመቶ የውጭ ንግድ እቀባ ይጣልባቸው ዘንድ የአሜሪካን ግምጃ ቤት ለውሳኔ አቅርቦታል፡፡
የሩቅ ምስራቅ እስያ ሀገራቱ ላዖስና ማይናማር ደግሞ ከፍተኛ የተባለው የ40 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ይጠበቃል፡፡
ካምቦዲያና ታይላንድ 36 በመቶ ሰርቪያና ባንግላዴሽ 35 በመቶ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካና ቦስኒያሄርዝጎቪኒያ የ30 በመቶ የውጭ ንግድ ታሪፍ ይጣልባቸው ዘንድ በስማቸው ትይዩ የሰፈረ አሀዝ ያመለክታል፡፡
14ቱም የትራምፕ አስተዳዳር የታሪፍ በትር የሚያርፍባቸው ሀገራት ምጣኔ ሃብታቸው በውጭ ንግድና ኢንቨስትምንት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ይህም የየሃራቱ ዋነኛ የንግድ መዳረሻ ከሆነችው ዋሽንግተን በኩል የሚኖራቸው አሉታዊ አሊያም አዎንታዊ የንግድ ትብብር በኢኮኖሚያቸው ላይ ሊያኖር የሚችለው አሻራ ጉልህ ነው፡፡
እነዚሁ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ያላቸው የንገድ ሽርክና ትራምፕ አንደሚሉት የተመጣጠነ የአሜሪካን ጥቅም ታሳቢ ያረገ ይሆን ዘንድ የአሜሪካ አምራችን አንዲያበረታቱ የሀገሪቱን ምሮቶች አብዝተውም እንዲጠቀሙ የሚደርግ ርምጃ እንዲወስዱ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህንን ያደርጉ ዘንድም በፕሬዚዳንት ትራምፕ ፊርማ የተደገፈ ደብዳቤ እንዲደርሳቸውም ተደርጓል፡፡
ይህን ማድረግ ካልቻሉም የውጭ ንግድ እቀባው ተግባራዊ እንደሚደረግም የነጩ ቤተመንግስት አስጠንቅቋል፡፡
የሲንጋፖሩ ብሄራዊ የስነ አስተዳዳርና ዘላቂነት ምርምር ማእከል ዋና ዳይሬክተር ሎውረንስ ሎህ፣ የትራምፕ አስተዳደር አስጊ የንግድ እቀባ ከፍራቻና ያልተፈለገ መዋከብ ይልቅ የነገ ህልውናን ታሳቢ ያደረገ ስክነት ይፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
ከፍተኛ የምርት መጠን የተነቃቃ ዕድገትና እመርታ እያሳዩ ያሉ ሀገራት የእርስ በእርስ የንግድ ትብብሮቻቸውን ማላቅ አማራጭ የንግድ መዳረሻ መፈለግ ላይ ሊተጉ ይገባልም ነው የሚሉት፡፡
አምራችና ሰፊ የንግድ ዕድል ያላቸው እስያዊያን ምሳሌ ያደርጋሉ፡ ሺ ኪሎሜትሮችን አማትረው ከአሜሪካ ጋ በሰቀቀን ከሚመሰርቱት ንግድ በተሻለ በእስያ አህጉር የዳበረና ጠንካራ ሽርክና መመስረት አዋጪው መፍትሄ ስለመሆኑም ለአልጀዚራ ምክረ ሃሳባቸውን አኑረዋል፡፡
በአቡ ቻሌ