የዓለም ሻምፒዮና በመጪው መስከረም ወር መጀመሪያ በጃፓን መዲና ቶኪዮ ለ20ኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡
ለስምንት ተከታታይ ቀናት በአጫጭር ፣ መካከለኛና ረጅም ርቀት እንዲሁም ሜዳ ተግባራት የአትሌቲክስ ውድድሮች ይከናወናሉ።
በቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና ለመሳተፍ የሚያስፈልገው ሰዓት (ሚኒማን) የዓለም አትሌቲክስ ቀደም ብሎ ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ለሚሳተፉባቸው ርቀቶች የተቀመጡ ሚኒማዎችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
በቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና በ800 ሜትር ለመሳተፍ ለሴቶች 1 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ እና ለወንዶች ደግሞ 1 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ ከ50 ማይክሮ ሰከንድ ሚኒማ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ እነዚህን የመግቢያ ሰዓታት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ ሴቶች ሊያሟሏቸው የሚችሉ ሰዓታት ናቸው፡፡
በ1 ሺ 500 ሜትር ለሴቶች 4 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ ከ50 ማይክሮ ሰከንድ ሲጠየቅ፤ ለወንዶች 3 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ መግቢያ ሚኒማ ተብሎ በዓለም አትሌቲክስ ይፋ ተደርጓል፡፡
በአምስት ሺ ሜትር ለሴቶች 14 ደቂቃ ከ 50 ሰከንድ ሲቀመጥ፤ ለወንዶች 13 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ የመግቢያ ሚኒማው ነው፡፡ በ10 ሺ ሜትር ለሴቶች 30 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ እንዲሁም ለወንዶች 27 ደቂቃ መሆኑ ይፋ ተደርጓል፡፡
በ3 ሺ ሜትር መሰናክል ሴቶች 9 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ እንዲሁም ወንዶች 8 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ ካላቸው በቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና መሳተፍ ይችላሉ ብሏል ዓለም አትሌቲክስ፡፡
ኢትዮጵያ ለሜዳሊያ በምትጠበቅበት ማራቶን ሴቶች እስከ 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ እንዲሁም ወንዶች እስከ 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ያላቸው ቶኪዮ ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ይፋ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈውን የማራቶን ቡድን ብቻ ነው ይፋ ያደረገው፡፡
በሌሎች ርቀቶች አትሌቶች ሚኒማ እንዲያሟሉ ቀነ ገደብ አስቀምጦ እየተወዳደሩ ይገኛል።
በሴቶች ማራቶን የቡዳፔስት አሸናፊዋ አማኔ በሪሶ በቀጥታ መሳተፏን አረጋግጣለች፡፡
የኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ትዕግስት አሰፋ፣ የቶኪዮ ማራቶን ባለ ድሏ ሱቱሜ አሰፋና የቦስተን ማራቶን የነሀስ ሜዳሊያ ባለ ድሏ ያለምዘርፍ የኋላው በቋሚ ተሰላፊነት እንዲሁም ትዕግስት ከተማ በተጠባባቂነት ተይዛለች፡፡
በወንዶች የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ታምራት ቶላ፣ ደሬሳ ገለታ እና ታደሰ ታከለ በተወዳዳደሪነት እንዲሁም ሚልኬሳ መንገሻ በተጠባባቂነት መያዛቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በታምራት አበራ