የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የስፖርት ማዘወተሪያ እና የህፃናት ማቆያ ስፍራዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማም ግንባታቸው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ማስመረቅ ችሏል፡፡
በክፍለ ከተማው ምቹ ያልነበሩ እና እደሳ የሚፈልጉ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች ተሰርተው ለሕብረተሰቡ ክፍት ሆነዋል፡፡
የማዘወተሪያ ስፍራዎቹ መመረቅ በተለይ ለታዳጊዎች ትልቅ የምስራች ሆኖላቸዋል፡፡
ሜዳዎቹ ከመሰራታቸው በፊት ለመጫወት ምቹ እንዳልነበሩ ታዳጊዎቹ አንስተዋል፡፡
ክረምት ሲመጣ ሜዳዎቹ ምቹ ባለመሆናቸው አስፓልት እና ድንጋያማ ቦታዎች ላይ ለመጫወት ይገደዱ እንደነበር የገለጹት ታዳጊዎቹ፣ ይህም ለአደጋ ያጋልጣቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
አሁን የተሰሩት ሜዳዎች ከምቹነታቸው በዘለለ ክረምት ላይም መጫወት ስለሚያስችሉ ደስታቸው ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ሀገራቸውን ወክለው የመሳተፍ ተስፋ እንዲኖራቸው እንዳደረገም ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በአራዳ ክፍለከተማ የተገነቡ የስፖርት ማዘወተሪያ እና የህፃናት ማቆያ ስፍራዎችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር እና የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ መርቀው ከፍተዋል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ