በበጀት ዓመቱ ከ366 ሺህ ለሚበልጡ ስራ ፈላጊዎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ::
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና የበጀት ዓመቱን ማጠቃለያ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባኤው የበጀት ዓመቱን የስራ አፈፃጸም ሪፖርት ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በበጀት አመቱ በስራ ዕድል ፈጠራ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ከተፈጠረው የስራ እድልም በከተማ ግብርና ዘርፍ 11 በመቶ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ 25.05 በመቶ እና በአገልግሎት ዘርፍ 63.95 በመቶ መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከተፈጠረው የስራ እድል ውስጥ ሴቶች 55 በመቶ፣ ወጣቶች ደግሞ 79.32 በመቶ ሲሆኑ፣ ምሩቃን 14.4 በመቶ የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎችም 27 ሺህ 293 ኢንተርፕራይዞች ከ5 ቢሊየን 132 ሚሊየን ብር በላይ ቁጠባ እንዲቆጥቡ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ለኢንተርፕራይዞች ብድር ለማመቻቸት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በበጀት ዓመቱ ከ 3.5 ቢሊየን ብር በላይ ማበደር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በታምራት ቢሻው