• ሚዲያው የከተማዋ ብልሹ አሰራሮች የሚታረሙበትን መድረክ
በማመቻቸት የልማቱ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ተገለፀ
መገናኛ ብዙሃን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለተደራሲያን የማድረስ ዋነኛ ዓላማ እና ኃላፊነት ይዘው ይመሰረታሉ፡፡ በየጊዜው ተደራሽነቱን እያሰፋ የመጣው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ለህብረተሰቡ ወቅታዊ፣ አስተማሪ፣ አዝናኝና አስጠንቃቂ መረጃዎችን የማድረስ ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ይገኛል፡፡
ሚዲያው በመረጃዎቹና ፕሮግራሞቹ ተከታታዮቹን ከማስገንዘብ በተጨማሪ በቀጥታ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ይወጣል፤ በተለይ በማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ለአብነትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ ረገድ ምሳሌ ሆኗል። የተቋሙን ሰራተኞች በማስተባበር በሚያገኘው ገቢ የበርካታ አዳጊዎችን የትምህርት ቤት ወጪ ይሸፍናል። በበዓላት ሰሞን በሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሮች ላይ አስተዋፅኦ ያደርጋል፤ በተለያዩ ጊዜያት በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ተገኝቶ እጅ ለአጠራቸው ወገኖች ደርሷል፤ በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከመደበኛው የሚዲያ ስራዎቹና ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ባሻገር ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ዜጎችን የሚያስገነዝቡ፣ የሚያስተምሩና የሚያነቁ ይዘቶችን በማዘጋጀት ተደራሽ ያደርጋል፡፡ በተለይ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠኑ ይዘቶችን ከተባባሪ አካላት ጋር በማዘጋጀት ለህብረተሰቡ የማድረስ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
ከሰሞኑም ከአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ በሁለቱ ተቋማት የተደረገው ስምምነት “ቤት አዲስ” የተሰኘ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በጋራ ለመስራት ነው፡፡ ፕሮግራሙ በየሳምንቱ የሚተላለፍ የ15 ደቂቃ ይዞታ ይኖረዋል፡፡

በውል ስምምነት መርሃ ግብሩ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፣ የትውልድ ድምፅ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ተቋሙን ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ እና ክፍተቶችን በመለየት ምላሽ እንዲያገኙ በትብብር እንደሚሰራ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀት እና በይዘት ሪፎርም እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የከተማዋ የጀርባ አጥንት እየሆነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ቢሮው የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት ወይዘሮ ቅድስት፣ እነዚህን ስራዎች ለማስተዋወቅ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ተመራጭ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በእስከ አሁኑ ሂደትም ቢሮው ለሰራቸው ስራዎች ሚዲያው ዐሻራውን ማሳረፉንም ጠቁመዋል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የከተማዋ ብልሹ አሰራሮች የሚታረሙበትን መድረክ በማመቻቸት የልማቱ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደምም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውም የሚታወስ ነው፡፡ ተቋማቱ በጋራ ለመስራት የተስማሙት “የሚሰሩ እጆች ወግ” የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲሆን፣ የስራ ባህል ለማዳበር ብሎም በቂ የስራ ዕድል የሚፈጠርበትን መደላድል መፍጠርን ያለመ ስለመሆኑም በተፈራረሙበት ወቅት መገለፁ ይታወሳል፡፡
በእርግጥ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከዚህ ቀደምም ከተለየዩ ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር ተፈራርሞ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ከከተማዋ እድገት ጋር አብሮ ከፍ እያለ የመጣው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በህትመት እንዲሁም በዲጂታል አማራጮች መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል። የትውልድ ድምፅ የሆነው ሚዲያው ተወዳደሪነት እና ተመራጭነቱን ለማሳደግ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች በማሳደግ የአድማጭ፣ ተመልካች እና አንባቢዎቹን ፍላጎት ለማርካትም እየተጋ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡
በ2023 ተመራጭ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ የመሆን ራዕይን የሰነቀው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በአዲሱ የኤ.ኤም.ኤን ፕላስ (AMN PLUS) የቴሌቪዥን ቻናሉ በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃዎችን ለህብረተሰቡ እያደረሰ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ