በጊዜው አማረ
ዳሩ ምንድ ነው የህይወት ውሉ
መኖር ካልቻለ አንዱ ለሁሉ
ጥንትም ከድሮ የመጣ እውነት
መተባበር ነው የኛ ማንነት… ይላል በእሱባለው ይታየው፣ ሳሚ ዳን (ሳሙኤል ብርሐኑ)፣ ቤቲ ጂ (ብሩክታዊት ጌታሁን) እና ዳዊት ጽጌ የተሰራው ሙዚቃ፡፡ ይህን ህብረ ዝማሬ በርካቶች ያውቁታል፡፡ ሙዚቃውን ሲሰሙ ልባቸው ይነካል። ይራራል፡፡ ለሌላ ወገን መድረስ እንዳለባቸው ያስባሉ፡፡ ምክንያቱም ኪነ ጥበብ በተለይ ሙዚቃ አንዱ ለሌላው እንዲደርስ፣ በጎነት እንዲስፋፋ፣ መረዳዳት ባህል እንዲሆን ትልቅ ሚና አለው፡፡
ኪነ ጥበብ ማህበረሰቡን ማስተማርና ማዝናናትን ጨምሮ መረዳዳትን ባህል ለማድረግ የማይተካ ሚና አለው፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ ይሰማራሉ፡፡ ሌሎችን ለበጎ ተግባር ያነሳሳሉ፡፡ ያነቃቃሉ፡፡ ያስተምራሉ፡፡ ሙዚቀኛው በመዝፈን፣ ሰዓሊው በስዕል ስራው እና በማስተማር ለማህበረሰብ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡
በሀገራችን በሙያቸው ከማገልገል አልፈው የኪነ ጥበብ ስራቸውን ለበጎ ፈቃድ አላማ የለገሱ የጥበብ ባለሙያዎች ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ወቅቱ ክረምት ነው፡፡ ክረምት በሀገራችን በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ይህንን መነሻ በማድረግ ኪነ ጥበብ በተለይ በጎ አድራጎትን ከማስተማር አንጻር ያለውን ፋይዳ እንደሚከተለው አዘጋጅቶታል፡፡
ኪነ ጥበብ የሰው ልጅ ስሜቱን፣ ሀሳቡንና ህልሙን የሚገልጽበት ጥንትም፣ ዛሬም ድረስ የዘለቀ ዘመናዊ መንገድ ነው። ሙዚቃ፣ ስዕል፣ ቴአትር፣ ግጥም እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች የህብረተሰብን ነፍስ የሚያድሱና የሚያነቃቁ ናቸው። በጎ ፈቃድ አገልግሎት ደግሞ በራሳችን ፍላጎት ለሌሎች የምናደርገው በጎ ተግባር ሲሆን፣ ማህበረሰብን የሚያጠናክርና የጋራ እድገትን የሚያመጣ ምሰሶ ነው። እነዚህ ሁለት የሚመስሉ ነገሮች በጥልቀት ሲታዩ፣ እርስ በርስ የሚደጋገፉና ማህበራዊ ለውጥን የሚያፋጥኑ የማይነጣጠል ቁርኝት አላቸው። ምክንያቱም አርቲስቶች በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የኪነ ጥበብ ስራዎቻቸውን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ፣ ድህነትን ታሪክ ማድረግ፣ የአካባቢ ጥበቃን፣ ችግኝ መትከልን፣ ትምህርት፣ የአረጋዊያን ቤት እድሳትን የመሳሰሉ መርሃ ግብሮች ላይ ተሳትፎ እንዲጨምር በዘፈን ወይም ድራማ ህብረተሰቡን በማነቃነቅ ለለውጥ እንዲተጋ ያደርጋሉ። የኪነ ጥበብ ኃይል ስሜትን የመንካትና መልዕክትን ከቃል በላይ የማስተላለፍ አቅም ስላለው በቀላሉ በጎ ተጽእኖ መፍጠር ይችላል፡፡
የሃበሻ ኳየር መስራችና የኪነ ጥበብ ባለሙያው ቢተው ዳዊት፣ “ኪነ ጥበብ ሌሎችን ከማስተማር፣ ከማነቃቃትና ከማስተባበር አቅሙ አንጻር በልኩ ያልተነገረለት እንዲሁም ያልተሰራበት ነው፡፡ ኪነ ጥበብ ትልቅ ሃይል ነው፡፡ ይህን ሃይል ደግሞ ለበጎ አድራጎት ስራዎች፣ ለልማት፣ ለመተጋገዝና ቀና ለሆኑ ጉዳዮች መጠቀም ይቻላል፤ ለአለብነትም ‘እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ’ የሚለውን የሙዚቃ ስራ መጥቀስ ይቻላል” ይላል፡፡
በእርግጥም ኢትዮጵያዊ አብሮነትን፣ መረዳዳት እና መተጋገዝን በብዙ የሙዚቃ ስራዎችና የኪነ ጥበብ ውጤቶች ተንጸባርቋል፡፡ ከላይ ከጠቀስነው ሙዚቃ የተወሰኑ ስንኞችን ስንመዝ፡-
ሰው እየረዳ በደግነቱ
ቁራሽ እንጀራ ለሌለው ቤቱ
መኖር ነው ያገር ሰው
ባህል እምነቱ
አንዱ ሲሞት ነው
ያንግዜ ሞቱ
እኔ ነኝ ደራሽ
ለወገኔ እኔ ነኝ
እሱ ነው እኔን
ሰው ያረገኝ ያቆመኝ…፡፡
በዓለም ላይ በርካታ የበጎ ፈቃድ ድርጅቶች ገንዘብ ለማሰባሰብ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን ያዘጋጃሉ። የጥበብ ትርዒቶች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የስዕል ሽያጭ እና የቴአትር ትዕይንቶች ለበጎ አድራጎት ስራዎች የገንዘብ ምንጭ ይሆናሉ። አርቲስቶችም በነጻ ተሳትፈው ለበጎነት ተግባር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ለምሳሌ፡- በሀገራችን በዚህ ወቅት የአረጋዊያን ቤት በስፋት የሚታደስበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ማለት ሙዚቀኞችና የሙዚቃ ባንዶች እንዲሁም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በአደባባዮችና በመዝናኛ ቦታዎች ስራዎቻቸውን በማቅረብ፣ ማህበረሰቡን በማነቃነቅ እና ለቤት እድሳት የሚውል ገንዘብ በመሰብሰብና አረጋዊያን ከክረምት ብርድና ፍሳሽ እፎይ እንዲሉ ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡
ሙዚቀኛ ቢተው እንደሚለው ለወገኑ ቀድሞ መድረስ ያለበት በቅርብ ያለ ወገኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ የሚለው ሙዚቃ ዘመን ተሻጋሪና በጎነትን በትክክል የሚገልጽ ነው፡፡
እኛም ሆነ ሌሎች ሙዚቀኞችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መሰል ስራዎችን መስራት አለብን፡፡ ምክንያቱም ኪነ ጥበብ ትልቅ አቅም አለው፡፡ የሰዎችን ስሜት መግዛትና ተጽእኖ ማሳረፍ ይችላል። ይህንንም በኮሪደር ልማቱ በተሰሩ የመዝናኛ ስፍራዎች ሙዚቃ ስናቀርብ መታዘብ ችያለሁ ሲል ያክላል፡፡
ፒተር ታሪየስ የተባሉ የዘርፉ ባለሙያ እ.ኤ.አ በ2024 ከኪነ ጥበብ ባለሙያው ቢተው ሃሳብ ጋር የሚቀራረብ ጽሑፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ “ነን ፕሮፊት” በሚል ገጸ-ድር ላይ ያሳተሙት ይህ ጽሑፍ “Volunteering opportunities that bring out the artist in you” የሚል ርዕስ አለው፡፡
ጸሐፊው እንደሚሉት፣ ኪነ ጥበብ ማህበረሰብን ከማነቃቃትና ከማስተማር አንጻር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የሰዎችን አእምሮ ያድሳል፡፡ ያነቃቃል። ስለዚህ አርቲስቶች ኪነ ጥበብን በመጠቀም በበጎ ፈቃደኝነት ሌሎችን ለመርዳት መስራታቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ምክንያቱም ኪነ ጥበብና ማህበረሰብ አብረው ነው የሚኖሩት፡፡ ጥበብና በጎ አድራጎት ደግሞ ሊነጣጠሉ አይችሉም። ስለዚህ በኪነ ጥበብ ማህበረሰብን ማገልገል፣ ራስን ማገልገል ነው፡፡
በእርግጥ አንዳንዶች ችግኝ መትከል፣ አረጋዊያንን መንከባከብ ግዴታ እንጂ እንደ በጎ አድራጎት መታየት የለበትም የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በፈቃደኝነት የምናከናውነው በጎ ስራ ነው ይላሉ። ይህንንም በማስረጽ የኪነ ጥበብ ድርሻ ትልቅ ነው፡፡ በተለያዩ ሀገራት አርቲስቶች ሙዚቃ በመጠቀም ለተጎዱ ወገኖች ይደርሳሉ፡፡ የአረጋዊያንን ቤት ያድሳሉ። የአካባቢ ጥበቃን ያበረታታሉ፡፡ የችግኝ ተከላ ስራዎችን ያስተዋውቃሉ፡፡ ማህበረሰቡን ይቀሰቅሳሉ፡፡ በእኛም ሀገር በቂ ነው ባይባልም መሰል ስራዎች ግን ተሰርተዋል፡፡ ወቅቱ ክረምትና የችግኝ ተከላ የሚካሄድበት ወቅት እንደመሆኑ የዛሬ 6 ዓመት በሀገራችን ኮሜዲያኖች ስለአረንጓዴ አሻራ ከተሰራው የማነቃቂያ ሙዚቃ ጥቂት ስንኞችን እንምዘዝ፡፡
በሰሜን በደቡብ
በምስራቅ በምዕራብ
መሐል ላይ ያላችሁ
የሀገሬ ልጆች እንዴት ከረማችሁ
እንደተለመደው መጥተናል መጥተናል
ቀልድ ብቻ አይደለም ችግኝም
ይዘናል፡፡
እኔም እዚህ፤ አንተ እዚያ ጋ
ጮማ እየቆረጥን ስንበላ ስጋ
ዛፍ መትከል አንዘንጋ….
እህት አበባ አንችም የእኛ ብርቱ
ከዚህ የበለጠ እንዳይሆን ሙቀቱ
ዛፍ መትከል ላይ በርቱ፡፡
“በጎ ፈቃደኝነትን በተመለከተ ትምህርታዊ የኪነ ጥበብ ስራዎች ዋጋቸው እልፍ ነው፡፡ አርቲስቶች እራሳቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ወይም በማህበረሰብ ፕሮጀክቶች ውስጥ በመሳተፍ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። አርቲስቶች ችሎታቸውን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲያውሉ፣ ሌሎችም በተለያዩ መንገዶች የበጎ ፈቃድ ስራ ላይ እንዲሳተፉ ያነሳሳሉ። ከዚህ አንጻር እኔም መቄዶንያ በመሄድ ተሳትፎ አድርጌያለሁ” ይላል ሙዚቀኛ ቢተው፡፡
ኪነ ጥበብ ሰዎች እንዲሰባሰቡና አብረው እንዲሰሩ ያነሳሳል። የኪነ ጥበብና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትስስር የህብረተሰባችን ብሩህ ተስፋ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ምክንያቱም ኪነ ጥበብን በመጠቀም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማጠናከር፣ ማህበራዊ ለውጥን ማፋጠንና የተሻለ ዓለም መፍጠር ይቻላል። የኪነ ጥበብን ኃይል ለበጎ ዓላማ በመጠቀም፣ የማህበረሰብን አኗኗር መለወጥና ዘላቂ ልማትን ማምጣት ይቻላል፡፡
ኪነ ጥበብ ማህበራዊ ጉዳዮችን እና ችግሮችን በግልፅ በማሳየት ሰዎች የበጎ ፈቃድ ስራ ያለውን አስፈላጊነት ግንዛቤ እንዲጨብጡ ያደርጋል። ለምሳሌ፣ ችግር የገጠማቸውን ሰዎች የሚያሳይ ልብ የሚነካ ሙዚቃ፣ ፎቶ ግራፍ ወይም ፊልም ቢሰራ ተመልካቾች በእነዚያ ሰዎች ጉዳይ እንዲነኩ እና የመርዳት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። አንድ ሙዚቀኛ አቅመ ደካሞችን ስለመርዳት ወይም ተፈጥሮን ስለመጠበቅ ወይም ችግኝ ስለመትከል ዘፈን ሲያቀርብ፣ ሌሎች ሰዎች የተጎዱት ወገኖችን ለመርዳት፣ በችግኝ ተከላና በሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያድርባቸዋል፡፡ የጋራ ለውጥ እና እድገት ማምጣት ይቻላል፡፡
ንዋይ ደበበ፣ አረጋሃኝ ወራሽ እና ፀጋዬ እሸቱ በጋራ በሰሩት ዘፈን፡-
መተዛዘን ቢኖር መረዳዳት ቢኖር
መተሳሰብ ቢኖር ሁሉም ቢተባበር
ሰው ለሰው ቢፋቀር ሁሉም ቢተባበር
የት ይደረስ ነበር…ያሉትም ለዚሁ
ነው።
በአጠቃላይ፣ ኪነ ጥበብ የበጎ ፈቃድ ስራን ለማበረታታት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ግንዛቤን በመፍጠር፣ አብሮነትን ከፍ በማድረግ፣ ተስፋን በመስጠት እና መድረክን በመፍጠር፣ ኪነ ጥበብ ማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል እንዲያደርግ ያግዛል። ስለዚህ መንግስታት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ግለሰቦች የዚህን ትስስር አስፈላጊነት ተረድተው በጋራ መስራት አለባቸው።