መገናኛ ብዙሃን የተመድ የሥርዓተ ምግብ ጉባኤን ሀገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ የተደራጀ መረጃ ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

You are currently viewing መገናኛ ብዙሃን የተመድ የሥርዓተ ምግብ ጉባኤን ሀገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ የተደራጀ መረጃ ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

AMN ሐምሌ 5/2017

መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን የተመድ የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ ሀገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ የተደራጀ መረጃ ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።

ኢትዮጵያ 2ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥርዓተ-ምግብ ጉባኤን ከሁለት ሳምንት በኋላ ታስተናግዳለች።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት መገናኛ ብዙሃን ጉባኤውን በተመለከተ ሊኖራቸው የሚገባው ግንዛቤ እና የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ፅንሰ ሀሳብ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎችን እያስተናገደች መሆኗን አውስተዋል።

የተመድ የሥርዓተ-ምግብ ጉባኤም ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻልና የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት እየሰራች ስላለው ስራ ለሌሎች ልምዷን የምታካፍልበት ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በስርዓተ ምግብ ሽግግር የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ልምድ የምትቀስምበት መሆኑንም አንስተዋል።

የምግብ አጀንዳ የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጉባኤው ያለውን ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት የተደራጀ መረጃ መስጠት የሚችሉበትን በቂ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ የተደራጁና ሙሉ መልዕክት የሚያስተላልፉ ዘገባዎችን በማቅረብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

የሚመለከታቸው ተቋማትም ለመገናኛ ብዙሃን መረጃን ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸው ሥራዎች ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ጉባኤውን እንድታስተናግድ መመረጧን ገልፀዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግርን ለማፋጠን እየሰራች ስላለው ስራና ስለ መጻኢ ተስፋዋ ለዓለም ማስተዋወቅ ያስችላታል ብለዋል።

ጉባኤው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን የተለየ ትኩረት ሰጥተው ተከታታይ ዘገባዎችን እንዲያሰራጩ መጠየቃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በምታስተናግደው የተባበሩት መንግስታት የሥርዓተ-ምግብ ጉባኤ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ የዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የግሉ ዘርፍን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉም ታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review