ደርጊቱ የተፈጸመዉ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ/ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አለም ባንክ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ ከቀኑ 11፡45 ላይ ነዉ፡፡
የቤት ሰራተኛ የሆነችው ሀብታሟ ወርቁ በመኖሪያ ቤት ውስጥ በስለት ተወግታ መሞቷን እና እህትማማች የሆኑ የአስርና የሰባት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህፃን እምነት አሽናፊ እና ጄሪ አሽናፊ መጥፋታቸው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ሪፖርት ይደሰርሰዋል፡፡
ጠቅላይ መምሪያው የፎረንሲክ ፣ የምርመራ እና የክትትል ቡድን አባላትን በማደራጀት ወንጀል ወደተፈፀመበት ስፍራ ከሄዱ በኃላ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ሥራው መጀመሩን የጠቅላይ መምሪያው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ገልፀዋል፡፡
የሟች ማንነት እንጂ የገዳይ ማንነት አለመታወቁ ፣ ሀብታሟን ማን ገደላት ? ህፃናቱስ የት ተሰውሩ ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እና ወንጀል ፈፃሚውን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንዲሁም የጠፉትን ህፃናት ለማግኘት ክትትሉ በቀጠለበት ሒደት መንግስቱ ደላሳ የተባለ ግለሰብ ለህፃናቱን ወላጅ እናት ለወ/ሮ ሃዊ ዮሴፍ ስልክ በመደወል ህፃናቱን ማገቱን 10 ሚሊዮን ብር ካልተሰጠው ልጆቹን እንደሚገድላቸው እንዲሁም ጉዳዩን ለፖሊስ ካሳወቀች በህፃናቱ ላይ የከፋ እርምጃ እንደሚወስድ የሚገልፅ መልእክት ያስተላልፋል፡፡

ህፃናቱ ከዚህ ቀደም አጋቹን ስለሚያውቁትና የደገሰላቸውን የሞት ድግስ ባለማወቃቸው ያለጭንቀት ሲጫወቱ እና ልጆቹ እርሱ ጋር መሆናቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ ለወ/ሮ ሃዊ ይልካል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ባደረጉት የክትትል ሥራ የፖሊስ አባላት ቀንና ሌሊት ባደረጉት ያላሰለሰ ክትትል አጋቹን እና ሌሎች ተባባሪዎቹን ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ/ም በቁጥጥር ስር በማዋል ሁለቱንም ህፃናት በአዳማ ከተማ ልዩ ቦታው ቦሌ ሰፈር እየተባለ ከሚጠራ አካባቢ ታግተው ከተቀመጡበት ቤት በሰላም ማስለቀቁን ኮማንደር ማርቆስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣዎችን ይዞ ምርመራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡
የህፃናቱ ወላጅ እናት ወ/ሮ ሃዊ ዮሴፍ እና አባታቸው አቶ አሸናፊ ጫኔ እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ በተፈፀመው የወንጀል ድርጊት በእጅጉ ተጨንቀው እንደነበር ተናግረው አዲስ አበባ ፖሊስ እና ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረጉት ጥረት ልጆቻቸውን በሰላም በማግኘታቸው በፀጥታ አካላት ተግባር ኩራት እንደተሰማቸው ገልፀዋል፡፡

ወንጀል ፈፃሚዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገው እንቅስቃሴ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም የኦሮሚያ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከታቸውን ለዚህም በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ስም ኮማንደር ማርቆስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
መሰል ችግር ሲያጋጥም ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ፖሊስ አስታውቆ ነገር ግን ልዩ ልዩ ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ስለ ወንጀሉ መረጃ ማሰራጨት ለወንጀል ፈፃሚዎቹ ምቹ ሆኔታን እንደሚፈጥር ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ተገቢው ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ