ጠላቶች በየአቅጣጫው ሀገሪቱን ለማፍረስ ሲያከናወኑ የነበሩትን የሽብር እንቅስቃሴን በመመከት በብዙ መልኩ ሰላም ተረጋግጦ ኢትዮጵያ ትላልቅ የልማት ዕድሎችን የሚታበስርበት ደረጃ ላይ መድረሷን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናገሩ፡፡
በቅርቡ የሚመረቀው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን እንዲሆን ሠራዊቱ ከደሞዙ ከማዋጣት ባሻገር የሕይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለውጤት ያደረሰ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነትን ለማስከበር ከኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ከክልል የፖሊስ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ ጠንካራ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረው በተከፈለው መስዋዕትነት ሃገሪቱ ዛሬ ላይ የተሻለ ሰላምና ደህንነት እንዲኖር አስችሏል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ጄይላን አብዲ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ይህንን የተናገሩት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃጸም የማጠቃለያ ግምገማ ላይ ነዉ፡፡
ሠራዊቱ አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችን አልፎ የሀገር ኢኮኖሚ ሊጎዱ የሚችሉ ከ20 ቢልየን ብር በላይ የሚገመቱ ወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በመያዝ ከፍተኛ ሥራ ማከናወኑን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በግምገማዉ ማጠቃለያ ላይ ገልጸዋል፡፡
የሃገሪቱን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ ሽብርተኞች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ጉዳያቸውን በማጣራት በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግና ሌሎች የሀገር ኢኮኖሚ ሊጎዱ የሚችሉ ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ መቻሉንም ጨምረዉ ገልፀዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል አያይዘው የተጠናቀቀዉ የበጀት አመት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሎጂስቲክ አቅም በእጅጉ ያደገበት፤ የዘመናዊ ትጥቆችና የሎጂስቲክስ ባለቤት የሆንበት፣ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ጭምር በቢሊየን የሚቆጠር ድጋፍ የተገኘበት፤ በዚህም የሃገሪቱ ፖሊስ ለማዘመን ውጤታማ ሥራ የተሰራበት እና የውጭ ግንኙነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና በማግኘት ተሸላሚ የሆነበት እንደነበር ተናግረዋል።
በወንድማገኝ አሰፋ