የአውሮፓ ህብረት ከዋሽንግተን ጋር በቀረጥ ዙሪያ የሚደረገው ውይይት የማይሳካ ከሆነ፣ ቀረጥ ሊጥልባቸው የሚችሉ 72 ቢሊየን ዩሮ ዋጋ ያላቸው የአሜሪካ ሸቀጦችን ዝርዝር ማውጣቱን አስታውቋል፡፡
የኅብረቱ የንግድ ኃላፊ ኮሚሽነር ማሮስ ሰፍኮቪች በብራስልስ ከህብረቱ ሚኒስትሮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ ከአሜሪካ የሚገቡ ቀረጥ ሊጣልባቸው የሚችሉ 72 ቢሊየን ዩሮ ዋጋ ያላቸውን ሸቀጦች የያዘ ዕቅድ አቅርበዋል።
ህብረቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ እስከ ፈረንጆቹ ነሐሴ 1 ድርድር የማያደርጉ ከሆነ፣ ከአውሮፓ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ30 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የአውሮፓ የንግድ ሚኒስትሮች ጎጂ ነው ያሉት ቀረጥ እንዳይጣልባቸው፣ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ አስቀድመው ከዋሽንግተን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ከዋሽንግተን ጋር ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቢቀር እና ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያስቀመጡትን ቀረጥ ቢጥሉ፣ ህብረቱ በተመሳሳይ ሁኔታ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ቀረጥ የማይቀር ከሆነ፣ በሁሉም ሚኒስትሮች ዘንድ እንደ አስፈላጊነቱ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን አለብን የሚል አንድ ዓይነት አቋም መኖሩንም የዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላርስ ሎክ ራስሙሰን ተናግረዋል፡፡
ህብረቱ ቀደም ሲል ትራምፕ በብረት እና በአሉሚኒየም ላይ ለጣሉት ቀረጥ ምላሽ ለመስጠት፣ 21 ቢልየን ዩሮ ዋጋ ያላቸው የአሜሪካ ሸቀጦችን ዝርዝር ማዘጋጀቱንም የአር ቲ ኢ ዘገባ አመላክቷል።
በታምራት ቢሻው