AMN ሀምሌ 10/2017 ዓ.ም
በኢራቅ ኩት ከተማ በገበያ ማዕከል ላይ በተከሰተ እሳት አደጋ የ60 ሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካቶች መጎዳታቸው ተገልጿል።
ከአምስት ቀናት በፊት ወደ ስራ በገባው በዚሁ ማዕከል ትናንት ምሽት የተከሰተው የእሳት አደጋ የበርካታ ዜጎችን ህይወት መቅጠፉ ነው የተነገረው። ይሁን እንጂ አሁን ላይ አደጋው በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተዘግቧል።
የፈረሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ የህክምና ባለሙያዎችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባው፣ 55 ሰዎች በቀጥታ በእሳት አደጋው የሞቱ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ድረስ የማቾች ቁጥር 60 ደርሷል።
የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተጨማሪ አስከሬን ፍለጋ ላይ መሆናቸው ተነግሯል።
የአካባቢው አስተዳደር መሃመድ አልሚያሂ አሳዛኝ አደጋ መድረሱን ገልጸው፣ የገበያ ማዕከሉ ባለቤት ላይ ምርመራና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
በኢራቅ ዜና አገልግሎት የወጣው የቪዲዮ መረጃ እንደሚያሳየው፣ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለማጥፋት በሚረባረቡበት ወቅት አደጋው ከአንዱ ወለል ወደ ሌላኛው ወለል ሲሰራጭ ተስተውሏል።
በሌሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች በተዘዋወረ ምስል ደግሞ የተወሰኑ ግለሰቦች ከህንፃው አናት እንዲሁም ከቃጠሎው መሃል ቆመው ታይተዋል።
አስተዳዳሪው አልሚያሂ የእሳት አደጋ ሰራተኞች የበርካቶችን ህይወት ማዳናቸውን ጠቁመዋል።
በቦታው እስካሁን አምቡላንሶች የከፋ ጉዳት በደረሰባቸውን 160 ኪሜ ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ባግዳድ ከተማ ለመውሰድ በጥድፊያ ላይ መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
የአደጋ ሰራተኞች አሁንም የጠፉ ሰዎችን ፍለጋ ላይ ናቸው።
ለአጃንስ ፍራንስ ፕረስ ሃሳቡን ያጋራው ዶክተር ናሲር አልቁረይሺ አምስት የቤተሰብ አባሉን በእሳት አደጋው ማጣቱን ተናግሯል።“
ከዚያም የአየር መቆጣጠሪያው በመፈንዳቱ ማምለጥ በማንችልበት ሁኔታ ወለሉን ሙሉ በእሳት ተያያዘ በማለት ሃዘናቸውን አጋርተዋል።
አንድ የህክምና ዶክተር በሰጠው ቃለ ምልልስ ‘ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሞታቸውንና በውል ያልተነሱ አስከሬኖች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በሄለን ተስፋዬ