በመዲናዋ እየተከናወነ ያለዉ የኮሪደር ልማት ትውልዱንና ዘመኑን የሚመጥን ስራ እንደሆነ ተገለፀ

You are currently viewing በመዲናዋ እየተከናወነ ያለዉ የኮሪደር ልማት ትውልዱንና ዘመኑን የሚመጥን ስራ እንደሆነ ተገለፀ

AMN – ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም

ከአራት ኪሎ ሽሮሜዳ እየተካሄደ ባለዉ የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛ እና የተሸከርካሪ መንገዶች እንዲሁም ሱቆችና የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡

ከእነዚህ መካከል በአምስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው የመዝናኛ ስፍራ ተጠቃሽ ነዉ፡፡

በአዲስ መልክ በተገለጠው አምስት ኪሎ ከድካማቸው አረፍ ለማለት በስፍራው ቆይታ ሲያደርጉ ያገኘናቸው መጋቢ ፍቃዱ ታደሰ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ መንበረ መድምም ትውልድና እድገታቸው በአዲስ አበባ ነው።

ላለፉት ረጅም አመታት ከተማዋን ጠንቅቀው የሚያውቋት ጥንዶቹ፣ የዓይን መነፅር ለማሰራት በስፍራው መገኘታቸውን ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል::

“ብቻዬን ብመጣ አላውቀውም ነበር” የሚሉት ወ/ሮ መንበረ፣ ሳቢ እና ምቹ ያልነበረው የአካባቢው የቀድሞ ገፅታ ሙሉ ለሙሉ ተውቦ ማየታቸው ግርምትን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ስፍራው በየትኛው የእድሜ ክልል ላሉ ነዋሪዎች ምቹ፣ ፅዱና ውብ ተደርጎ ከነማረፊያው ጭምር መሠራቱ የመንፈስ እርካታን የሚያላብስ ድንቅ ስራ መሆኑንም አክለዋል።

በቀደመው ጊዜ ህፃናትን፣ አረጋውያንን፣ ሴቶችን፣ እናቶችንና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ መሠል የማረፊያም ሆነ የመዝናኛ ስፍራን የያዘች አዲስ አበባ መመልከት ህልማቸው እንደነበር መጋቢ ዶ/ር ፍቃዱ አስረድተዋል።

አሁን ላይ ለኔም ሆነ ለሌሎች አበርክቷቸው ከፍተኛ የሆኑና የነዋሪውን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የልማት ስራዎች በጥራትና በፍጥነት መሠራታቸው የከተማዋን የእድገት ጉዞ ያመላክታል ብለዋል።

ሁሉን አካታች ሆኖ የተሰራው የኮሪደር ልማት ትውልዱንና ዘመኑን የሚመጥን፣ ሠውና ተፈጥሮን ያወዳጀም እንደሆነ አንስተዋል።

አካባቢው እንዳማረበት ለትውልድ እንዲሻገር ህብረተሰቡ ስፍራውን በባለቤትነት ሊጠብቅ እና ሊንከባከብ ይገባል ሲሉም ጥንዶቹ አፅንኦት ተናግረዋል፡፡

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review