አሁን በሥራ ላይ ያለው ሥራ አስፈፃሚ እስከ ነሐሴ 30 በኃላፊነት ይቀጥላል ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 3ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ዛሬ አካሂዷል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት 3ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ እንደተናገሩት፤አሁን በሥራ ላይ ያለው ሥራ አስፈፃሚ ከዛሬ 3 ዓመት ሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ህዝብ ሙስሊሙን ለሶስት ዓመታት ሲያገለግል ቆይቷል።

በዚህም ወቅት ስኬታማ የሆኑ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የትምህርትና ማህበራዊ አገልግሎት ዳይሬክተር አኑዋር ሙስጠፋ፤ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በቀሪ ጊዜያት በየመስጂዱ በመመዝገብ የሚወክሉ ተወካዮች እንዲመርጥ በአቋም መግለጫው ገልፀዋል።
የምርጫ አስፈጻሚ ቦርዱ ስራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ መጠየቁን በአቋም መግለጫው የተጠቆመ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በየእርከኑ በስራ ላይ የሚገኘው የመጅሊስ ጠቅላላ ጉባዔና ስራ አስፈፃሚ የስራ ዘመን እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም መወሰኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ለሚካሄደው ምርጫ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ በመግለጫው ተጠይቋል።