በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎች መዲናዋ የኮንፍራንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ያስቻሉ መሆናቸዉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።
138 ሀገራት ኤምባሲያቸውን በአዲስ አበባ ከተማ መክፈታቸውን የተናገሩት አምባሳደሩ መዲናዋ ለረጅም ዘመን የአፍሪካ መዲና በሚለው ስያሜ እንድትታወቅ አስችሏታል ብለዋል።
ከተማዋ ተመራጭ የዲፕሎማቲክ መናኸሪያ ብቻም ሳትሆን ከኒውዮርክና ከጄኔቭ ከተሞች በመቀጠል ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በብዛት የሚካሄዱባት መሆኗንም አብራርተዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማዋ የተገነቡት መሰረተ ልማቶች የከተማዋን ዓለም አቀፋዊነት ያጎሉ መሆናቸዉን የተናገሩት ቃል አቀባዩ መዲናዋን ለነዋሪዎችም ሆነ ለጎብኝዎች የምትመች ከተማ ለማድረግ የተጀመሩትን ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
በመዲናዋ የታየዉ ለዉጥ በቅርቡ በተካሄደው የህብረቱ ጉባኤ የተገኙ መሪዎች የሰጡት ምስክርነት ብቻም ሳይሆን ተሞክሮውን ለመውሰድ የጠየቁ ወዳጅ ሀገራት ቋሚ ምስክሮች ናቸው ብለዋል።
አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው አዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ሴንተር ከሌሎች ልማቶች ጋር ተዳምሮ ከተማዋ የምታስተናግደው ኮንፈረንስ አቅም እንዲጨምር አስችሏል፣ መዲናዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ስበት ማዕከልነትም አሳድጓል፡፡
ይህም ለተለያዩ ስብሰባዎች የሚመጡ መሪዎችንም ሆነ ከባለሀብቶች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡
በሚካኤል ህሩይ