ዛሬ የተመረቁት 150 የትምህርት ፕሮጀክቶች በታማኝነት የማገልገል እና የትጋት ዉጤቶች መሆናቸዉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ትውልድን መገንባት ቀዳሚው ሥራችን ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም በእርጅና ብዛት የተጎሳቀሉ እና ለመማር ማስተማሩ ሂደት እንቅፋት የፈጠሩ፣ በሂደትም በተማሪዎቻችን የ12ኛ ክፍል አጠቃላይ ዉጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠሩ እና የትምህት ጥራት ያጓደሉ ችግሮችን ቀርፈን በአጭር ጊዜ 6ኛ እና 8ኛ ክፍልን ጨምሮ በ2ኛ ደረጃ የተማሪዎቻችን አበረታች ዉጤት አስመዝግበናል ።
የተሻሻሉ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መፃህፍትና ቤተ ሙከራ፣ የህፃናት ማረፊያ፣ ፅዱና አረንጓዴ ቅጥር ጊቢ፣ የስፖርት ማዘዉተሪያ ያላቸዉን የትምህርት መሰረተ ልማቶች እያስፋፋን እንገኛለን። የተቀናጀና የተናበበ እቅድ በመንደፍ የስራ ባህላችንን በማሻሻል በሰራናቸው ስራዎች ውጤታማ ሆነናል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር የከተማዋን የትምህርት ተደራሽነት ለማረጋገጥ እና የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል በያዘው እቅድ ባለፉት አምስት ዓመታት 110 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። በነባር ትምህርት ቤቶች ውስጥ የማስፋፋያ ስራ በመስራትም ከ30 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት እና 334 መመገቢያ አዳራሾች፣ 206 ቤተ ሙከራ እና ቤተመጽሐፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ መገንባት ችለናል። እንዲሁም ትምህርት ቤቶች አካታች፣ ምቹ፣ ውብና ንፁህ፣ የደህንነትና የውበት ደረጃን የጠበቀ አጥር መገንባት ተችሏል፡፡
በዚህ ስራ ለይ በመሳተፍ ትውልዱ ላይ መልካም ዘርን የዘራችሁትን ሁሉ ላመሰግን እወዳለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡