የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 90 ቀናት 450 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ ይገኛል
አመሻሻ ላይ ነው፤ በግምት 11 ሰዓት ገደማ ሆኗል፡፡ ለመጥለቅ እየዳዳች ካለችው ጀንበር የሚፈልቀው ብርቱካናማ ብርሃን በነፋሻማው የሲ.ኤም.ሲ ሰማይ ላይ ናኝቷል፡፡ በተለምዶ ሲ.ኤም.ሲ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከመሪ ወደ ደራርቱ አደባባይ በሚወስደው መንገድ አንድ በእድሜ ጠና ያሉ አባት ይራመዳሉ። በአግራሞት የመንገዱን ግራና ቀኝ ደጋግመው ያማትራሉ፡፡ ይህ መስመር የኮሪደር ልማት ከተከናወነባቸው የከተማዋ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ ቀላል የከተማ ባቡር ሐዲድ በሁለት የከፍለው አውራ ጎዳና በሁለቱም መስመር በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ጎን ለጎን ያስኬዳል፡፡
የአውራ ጎዳናው ሁለቱም ጎን በእጅጉ ተውቧል፡፡ በቀይ እና አረንጓዴ ቀለማት ያሽበረቀው የብስክሌት መስመር፣ ሰፊው የእግረኛ መንገድ፣ የሳር ንጣፍና እፅዋት፣ የህንፃዎቹ የቀለም ቅብ፣ በአጭር ርቀት ልዩነት በአማሩ መቀመጫዎችና ደረጃዎች ተውበው የሚገኙ መናፈሻዎች፣ ዘመናዊነት የሚታይባቸው የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ተርሚናሎች ለአካባቢው ልዩ ድባብ አላብሰውታል፡፡ ይህ የአካባቢው አዲስ ገፅታ በአቶ ነጋሽ ደበበ አንደበት እንዲህ ይገለፃል፡፡
አቶ ነጋሽ ደበበ ከመገናኛ ወደ ደራርቱ አደባባይ በሚወስደው መስመር ላይ የእግር ጉዞ የሚያደርጉት አግራሞት በተሞላበት አኳኋን የመንገዱን ግራና ቀኝ አብዝተው እያማተሩ ነው፡፡ ከሰላምታ ልውውጥ በኋላ፣ “ለአካባቢው እንግዳ ነዎት?” የሚል ጥያቄ በመሰንዘር ለውይይት ጋበዝኳቸው፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት በዚሁ አካባቢ እንደኖሩና በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት አካባቢው የተጎናፀፈው ገፅታ ከጠበቁት በላይ እንደሆነባቸው አድናቆት በሚንፀባረቅበት አኳኋን ያወጉኝ ጀመር፡፡
የቀድሞውን ገፅታ እያስታወሱ ከአሁኑ ጋር አነፃፅረው ሲናገሩ፣ “በፊት የመኪናው መንገድ ጠባብ ነበር፡፡ እሱም ለባቡር ሐዲድ ተብሎ ተቀነሰ፡፡ በቂ የእግረኛ መንገድ አልነበረም፤ እርሱም ቢሆን በጎዳና ላይ ነጋዴዎች ተይዞ ስለነበር በእግር መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፤ ከዚሁ የተነሳ ሰው ከቤቱ ወጥቶ በእግር ለመንቀሳቀስ አይደፍርም፡፡ አሁን ከመንገዱ መስፋት ባለፈ አካባቢው ላይ የነበሩ አላስፈላጊ ግንባታዎች ተነስተው፣ አላግባብ የታጠሩ ክፍት ቦታዎችም አጥራቸው ተነቅሎ ግልፅና ክፍት የህዝብ መዝናኛዎች ሆነዋል፡፡ ይህም ከስጋት ነፃ የሆነ አካባቢ እንዲሆን አድርጓል። ወንጀል ተወግዷል። ሽፍንፍኑ ተገልጦ አሁን ሁሉም ነገር ፊት ለፊት የሚታይ ሆኗል፡፡” ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት አጋርተውናል፡፡
ከአቶ ነጋሽ ጋር በነበረን አጭር ቆይታ ከአነሷቸው ነጥቦች መካከል “ከህዝብ የተሰበሰበ ግብር ተመልሶ ለህዝብ ጥቅም እየዋለ ነው፡፡ ይህ ዘመኔን በሙሉ ስመኘው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡” በሚል መንደርደሪያ ትልቅ መልዕክት ያለው ቁም ነገር አጋርተውኛል፡፡
ሀሳባቸው ቃል በቃል ሲቀመጥ፣ “ደክሜ ከማገኘው ገቢ ለመንግስት የሚገባውን ግብር አስቀርቼ አላውቅም። ነገር ግን በዚህ ገቢ ህዝብን ታሳቢ ያደረጉ በቂ የልማት ስራዎች አይሰሩም የሚል ቅሬታ ነበረኝ፤ አሁን ቅሬታዬ በእርካታ ተተክቷል፡፡ ግብሩ በትክክልም መልሶ የግብር ከፋዮቹ መጠቀሚያ ሆኗል። ለዚህም ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የመሰለ መሻሻል በከተማዋ እየታየ ያለው።” ይላል፡፡
ይህም ለመሆኑ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የግብር አሰባሰብ ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚሰበሰበው ገቢና የልማት ስራው ትስስር በምን ሁኔታ ይገኛል? በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ የሚያጠነጥን ፅሑፍ ለማዘጋጀት አነሳሳኝ፡፡
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ካሉ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አንዱ በሆነው ወረዳ 13 አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ግብር ከፋይ የሆኑት ወይዘሮ ስሜነሽ ግዛው የተባሉ አስተያየት ሰጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግብር አሰበሰብ ስርዓቱ እየዘመነና እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም የግብር ከፋዩን ድካም የሚቀንሱና ጊዜን የሚቆጥቡ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮች በስፋት ተደራሽ መሆናቸው ጊዜአችንን በአግባቡ ለመጠቀምና ስራ ላይ አውለነው የተሻለ ገቢ ለማግኘት አስችሎናል ይላሉ፡፡
አሁን ላይ ወደ ግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት መሄድ ሳይጠበቅባቸው በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በአጭር የፅሑፍ ማሳወቂያ ተገልፆላቸው በሞባይል ባንኪንግ፣ በቴሌ ብር ወይም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚከፍሉበት አሰራር መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሚያጋጥሙ ችግሮች አንዱ የግብር አከፋፈሉ በባንክ የሚፈፀም ባለመሆኑ ግብር ለመክፈልም ሆነ ለማሳወቅ ረጅም ሰልፍና ምልልሶች እንደሚያጋጥሙ አንስተው፣ ይህን ችግር ለመፍታት የተዘረጋው አስራር በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክፍለ ከተማው ወረዳ 3 የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋይ አቶ ፉአድ ቢላል በበኩላቸው፣ ግብርን በወቅቱና በአግባቡ መክፈል የዜግነት ግዴታ ብቻም ሳይሆን የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተሰማሩበት የሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ሰርተው ከሚያገኙት ትርፍ ግብራቸውን በወቅቱና በአግባቡ ሲከፍሉ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡
ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ተቆርቋሪነት በተግባር ከሚያሳዩባቸው መገለጫዎች መካከል አንዱ ታማኝ ግብር ከፋይነታቸው ስለመሆኑ እሙን ነው። ግብርን በወቅቱና በአግባቡ መክፈል የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን የስልጣኔ መገለጫም ነው፡፡ ዜጎች በፍቃደኝነት የሚከፍሉት ግብር ተመልሶ ለልማት ብሎም ለራስ ጥቅም የሚውል በመሆኑ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ያለማንም ጎትጓች የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱና በአግባቡ መክፈል እንዳለበት ይታመናል፡፡
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ከድር ሲራጅ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ በክፍለ ከተማው ከ60 ሺህ የሚበልጡ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል 25 ሺህ 522 ያህሎቹ ከንግድ ትርፍ ግብር የሚከፍሉ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የአጠቃላይ የግብር ከፋይ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደሚሄድ ያስታወሱት ስራ አስኪያጁ በክፍለ ከተማው በየዕለቱ አዳዲስ ንግድ ፍቃድ የሚያወጡ ደንበኞች መኖራቸውንና አሁን ላይ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችን ጨምሮ 34 ሺህ 785 የአከራይ ተከራይ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
እነዚህን ግብር ከፋዮች በአግባቡ ለማስተናገድ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንና በተለይ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚጠበቅባቸውን ግብር ማሳወቂያና የመክፈያ ጊዜ እንደመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
እንደ አቶ ከድር ገለጻ፣ የሰው ኃይልን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ ለውሳኔ ዝግጁ ማድረግና የተለያዩ መረጃዎቸን የማደራጀት ብሎም ግብር የሚከፍሉና ያቋረጡትን የመለየት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በዝግጅት ምዕራፉ ትልቁ ትኩረት የነበረው ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ካለው የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በተደረገ ውይይት የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው ያሉት ስራ አስኪያጁ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ በ90 ቀን እቅድ በማካተት ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በታክስ አዋጁ እንደተቀመጠውም ደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 እንዲሁም ደረጃ ‘ለ’ ከሐምሌ 1 እስከ ጳጉሜ 6 የሚከፍሉ ሲሆን፣ በተለይም የጥቅምት ወር እንደ ከተማ ከፍተኛው ግብር የሚሰበሰብበት የደረጃ ‘ሀ’ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን የሚያሳውቁበትና የሚከፍሉበት ወቅት ይሆናል፡፡
ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የተሻለና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በየጊዜው ግንዛቤ ከማስጨበጥ ብሎም አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን ጥረት ተደርጓል። የግብር ከፋዩን ድካም የሚቀንሱና ጊዜን የሚቆጥቡ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የውሳኔ አሰጣጡን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን፣ ባሉ የመክፈያ መንገዶች ያለምንም የሰው ንክኪ ክፍያቸውን እንዲፈፅሙ ተደርጓል፡፡
ከእነዚህም የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር ለማወቅና ለመክፈል ወደግብር ሰብሳቢው ተቋም በአካል ሳይሄዱ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በአጭር የፅሑፍ ማሳወቂያ ተገልፆላቸው በሞባይል ባንኪንግ፣ በቴሌ ብር ወይም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚከፍሉበት አሰራር መመቻቸቱ ተጠቃሽ ነው፡፡
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በሐምሌና ነሐሴ ወር የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ሲሆን፣ በእነዚህ ወቅቶች የ90 ቀናት እቅዱን ጨምሮ 450 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ከዚህም 238 ሚሊዮኑ ከደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የሚሰበሰብ ነው፡፡ ቀሪው ከመደበኛ ወርሃዊ ገቢ፣ ከደመወዝና ከተለያዩ ገቢዎች የሚሰበሰብ መሆኑንና በሂደት ታይቶ ሊጨምር እንደሚችል ነው አቶ ከድር የሚገልፁት፡፡
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ መገርሳ በበኩላቸው፣ በወረዳው ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የግብር ግዴታቸውን መወጣት ያለባቸው 4 ሺህ 600 የሚጠጉ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች አሉ፡፡ እነዚህ ግብር ከፋዮች በተጠቀሰው ጊዜ እንዲከፍሉ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የቅስቀሳ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከቅስቀሳ ስራው ጎን ለጎን በሐምሌ ወር የሚሰበሰበው የደረጃ ‘ሐ’ ግብር አሰባሰብ እንደከተማ ከወረደው የ90 ቀን እቅድ ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቅቀው ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ