በዓመቱ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 150 የትምህርት ፕሮጀክቶች መከናወናቸው ተጠቆመ
ፕበቀደሙት ዓመታት ደካማ እና ስሁት በሆነ ፖሊሲ ክፉኛ ከተጎዱ ዘርፎች መካከል ትምህርት አንዱ ነው። በተለይ ኢህአዴግ ቀርጾ ሲተገብረው የቆየው ፖሊሲ በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ስለማድረሱ ተደጋግሞ ይነገራል። ነገር ግን ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በተወሰዱ ተከታታይ የማስተካከያ እርምጃዎች ዘርፉ ላይ መሻሻል መጥቷል።
በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 150 የትምህርት ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቀዋል፤ በ2018 ትምህርት ዘመን ወደ ተሟላ አገልግሎት እንደሚገቡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ያሰፈሩት መልዕክትሮጀክቶቹ ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው የተሰሩ 14 አዳዲስ ትምህርት ትቤቶች፣ 64 ነባር ትምህርት ቤቶች ላይ በማስፋፊያ ስራ የተገነቡ 1 ሺህ 655 የመማሪያ ክፍሎች፣ የአይ.ሲ.ቲ ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራዎች፣ የመመገቢያ አዳራሾች፣ ቤተ መፅሐፍቶች፣ የስፖርት ሜዳዎች፣ ምድረ ጊቢዎችን ፅዱና ውብ የማድረግ ስራ፣ የመጸዳጃ ቤቶች እና የውሃ አገልግሎትን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እና መምህራን ምቹ የማድረግ ስራዎችን ያካተቱ ስለመሆናቸው ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች በመልዕክታቸው ጠቁመዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ለትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች የ2017 የትምህርት ዘመን እቅድ አፈጻጸም ግምገማዊ ስልጠና እና የ2018 ዓ.ም እቅድ ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ የስራ አቅጣጫ የሰጡት የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፣ በ2017 የትምህርት ዘመን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፣ በዚህም ቀላል የማይባል ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም በየትምህርት ቤቱ የተካሄደው ድጋፍና ክትትል የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ማበርከቱን የጠቆሙት ዘላለም (ዶ/ር)፣ በከተማ አስተዳደሩ በዘንድሮው ዓመት በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል የተመዘገበው አበረታች ውጤትም ሆነ በከተማ ደረጃ ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ተሰጥቶ በስኬት የተጠናቀቀው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዘርፉ ላይ ሲሰራ የነበረው ተከታታይ ማሻሻያ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ዘላለም (ዶ/ር)፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ ይህም ለመጣው ውጤት አንዱ ምክንያት ይሆናል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የተከናወኑባቸው ክፍለ ከተሞች በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ረገድ ከቀደሙት ዓመታት ግልፅ ልዩነት እንደሚያመጡም ተመላክቷል፡፡ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ለሊስቱ ተስፋዬ፣ በክፍለ ከተማው በ18 ተቋማት የተገነቡ 50 የትምህርት ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቶቹ ለትምህርቱ ዘርፍ መሻሻል የጎላ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ መሃል ከተማ የነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ክፍለ ከተማው መምጣታቸውን ተከትሎ በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ቁጥርም መጨመሩን ጠቅሰው፣ የተማሪዎች የክፍል ጥምርታ፣ የመፀዳጃ ቤት እንዲሁም ለመማር ማስተማሩ ምቹ የሆነ መሰረተ ልማት ከመፍጠር አኳያ የፕሮጀክቶቹ መመረቅ በርካታ ችግሮችን ይፈታሉ ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በአንድ ክፍል ከ70 እስከ 130 የሚደርሱ ተማሪዎች ይማሩ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዋ፣ ችግሩን ለማቃለል በቆርቆሮ በተሰሩ የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ እስከመማር ተደርሶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
አሁን የተከናወኑት የማስፋፊያና አዳዲስ ግንባታዎች የተማሪና የክፍል ጥምርታ ከማስተካከል ባለፈ ተማሪዎች ሰፊና በተመቻቸ ሁኔታ የሚማሩበትን ዕድል የሚፈጥር ብሎም የተማሪዎች የክፍል ጥምርታንም ወደ 50 እንደሚያደርሰው አስታውቀዋል፡፡
በተለይ በገላን ጉራ የልማት ተነሺዎች መንደር የተገነባው አብዲ ጃርሶ ትምህርት ቤት ለልማት ተነሺዎች የመማር ማስተማሩን ሂደት በተሳካና በተመቻቸ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ይሰጥበታል፡፡
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በመንግስት የተቋቋሙ 10 ሁለተኛ ደረጃ፣ 17 አንደኛ ደረጃና 17 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ሲኖሩ፣ የእነኝህም የቅበላ አቅም ከ1 ሺህ 500 እስከ 1 ሺህ 800 የሚደርስ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁት እነዚህ ግንባታዎች በርካታ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው የተማሪዎችንም ሆነ የማህበረሰቡን ችግሮች የፈቱ በትምህርት ጥራት ረገድም ከፍተኛ ፋይዳ የሚያመጡ ናቸው፡፡
የ2017 የትምህርት ዘመን በክፍለ ከተማው ያሉ የግል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በቀንና በማታው ክፍለ ጊዜ ወደ 200 የሚጠጉ ተማሪዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ኃላፊዋ ከፕሮጀክቶቹ ምረቃ በኋላ ግን የተማሪ ቅበላ በእጅጉን እንደሚጨምር ነው የጠቆሙት፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ነጋሽ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በትምህርት ዘርፍ ብቻ ወደ 16 ግንባታዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ እነኝህም ከዚህ በፊት የነበረውን የተማሪ ክፍል ጥምርታ 1 ለ 45 በማመጣጠን፣የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
ትናንት ከተመረቁት በርካታ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው በክፍለ ከተማው ወረዳ 14 ሃና ፉሪ የተገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ርቀው ሳይሄዱ በአቅራቢያቸው የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ ነው ያሉት ኃላፊው ወደ 15 ሺህ ካሬ ሜትር በሚጠጋ መሬት ላይ በተከናወነው በዚህ ፕሮጀክት በርካታ የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሁለት ባለ አራት ፎቅ፣ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች መማሪያ፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ ስፖርት ሜዳና የአስተዳደር ህንፃዎችን ማካተቱን ጠቅሰዋል፡፡
ዘላለም (ዶ/ር) በማብራሪያቸው “ከጊዜ ወደ ጊዜ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ እያመጣን ያለነው እመርታዊ ለውጥ ይበል የሚያሰኝ ነው” ብለው፣ በትምህርት አመራር፣ በመምህራን፣ በትምህርት ባለሙያው፣ በአሰራሩ፣ በአደረጃጀትና በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ያሉ ህፀፆችና ግድፈቶችን በተደራጀ ስልት መቅረፍ ይገባል፤ ባለፉት ዓመታት ይህን ስናደርግ ነበር ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ትምህርት ክፍል መምህር ውቤ ካሳዬ (ዶ/ር) ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ፣ በትምህርት ዘርፉ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ነባር ችግሮችን በማቃለል የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን የማረጋገጥ ዕድል እንደሚሰጡ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
መምህሩ በሰጡን አስተያየት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በትምህርት ዘርፍ ላይ የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የሚሄድ ውጤት ያስገኛሉ፡። በተራዘመ ጊዜ ደግሞ ከችግሩ በመውጣት ጠንካራና ተወዳዳሪ ትውልድን የማፍራት አቅም ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የታየው ውጤትም ችግሮቹ እየተቃለሉ እንደሚሄዱ አመላካች ናቸው ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እንደ ዩኒፎርም፣ ጫማ፣ ደብተር እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦትን ለተማሪዎች በማመቻቸቱ የትምህርት ጥራት ላይ የነበሩ ክፍተቶች እየተሞሉ መምጣታቸውን የጠቆሙት ዘላለም (ዶ/ር)፣ በተለይም የምገባ መርሃ ግብሩ የተማሪዎችን ውጤታማነት አሳድጓል፡፡ የትምህርት አቀባበል አቅማቸው ላይም ልዩነት አምጥቷል የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
“በቀዳማይ ልጅነት ላይ የሚደረገው ርብርብም ሌላ አቅም የሚፈጥር ዕድል ነው። በተጨማሪም የቅድመ 1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የማስተማር ስነ ዘዴ ጨዋታን መሰረት ያደረገ መሆኑ ተማሪዎች ለቀጣዩ እርከን ዝግጁ እንዲሆኑ በማስቻል ለትምህርት ጥራት መሻሻል አግዟል” ብለዋል፡፡
እንደ ዘላለም (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ በእንግሊዘኛና ሒሳብ ትምህርቶች ላይ የነበረውን ክፍተት ለመድፈን እስትራቴጂ ተነድፎ በጥብቅ ዲሲፕሊን መተግበሩ ለውጤቱ መሻሻል ያበቃ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በ2017 የትምህርት ዘመን የመጣው መሻሻልም የዚሁ ጥረት ውጤት ነው፡፡
በከተማዋ ካሉ ተማሪዎች መካከል ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት በመንግስት ትምህርት ቤቶች ይማራሉ። በትምህርት ቤቶቹ ያሉት ጫናዎች ማቅለል ላይ እየተሰራ ነው፡፡ ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት በሚችልበት ልክ እየተሰራበት ነው፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ