ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ እሴቶች መገኛ ነች፡፡ እነዚህ ባህላዊ እሴቶች የማህበረሰቡን አንድነትና አብሮነት ከማጠናከር ረገድ ያላቸዉ ሚና የጎላ ነዉ፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ባህላዊ እሴቶች መካከል ደግሞ በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ በስፋት የሚታወቀዉ ማር መጎራረስ ባህል ተጠቃሽ ነዉ፡፡
በጎፋ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት የኮሚኒኬሽንና ሚዲያ ዳይሮክተሬት ዳይሬክተሩ አቶ ገነነ እንዳሻዉ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት ማር መጎራረስ በአካባቢዉ አጠራር “ማል-ኤሶ” የህዝቦች አንድነት ፤ ህብረት ፣ወዳጅነትና ፍቅርን የሚጠናከርበት ባህላዊ እሴት ነዉ፡፡
በማል-ኤሶማር የተጎራረሱ ሰዎች ከተጎራረሱበት ዕለት ጀምሮ በስም አይጠራጠሩም ይላሉ አቶ ገነነ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማር በመጎራረስ እርስ በርስ ላለመለያየት ወዳጅነትን ስላጠናከሩ “ማል-ኤሶ” ተባብለው ነው የሚጠራሩት ይላሉ፡፡
የሚያስደንቀው ነገር ደግሞ በማል-ኤሶ አንደ ማር በመጎራረስ ወዳጅነት ከፈጠሩ ጓደኞች አንደኛው በሞት ቢለይ እና ጓደኛው በተቀበረበት መቃብር አጠገብ በድንገት ሌላኛው ጓደኛ ቢደርስ ቆም ብሎ “ማል-ኤሶ_ታ ኤሶ” የኔ ማር፣ የኔ ወዳጅ ብሎ ነው የሚያልፈው ምክንያቱም ወዳጅነታቸውን ሁሌም ያስበዋል፣ ያስታውሰዋል በማለት ገልጸዋል፡፡
ማር የመጎራረስ መርሃ ግብሩም የተለያዩ ሁነቶች ሲኖሩ እንደሚተገበርም ጠቅሰዋል፡፡
የወዳጅነት መገለጫ የሆነዉን ማር የመጎራረስ ባህል ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ገነነ እንዳሻዉ ሰሞኑን “ማል-ኤሶ” ማር የመጎራረስ መርሃ ግብር በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ