ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ያለምንም የውጭ ዕርዳታም ሆነ ብድር መቶ በመቶ በራስ ዓቅም በመንግስትና ህዝብ የተገነባ መሆኑ ተገለጸ።
በ2017 በጀት ዓመት ለግድቡ 1.7 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
የማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በበጀት ዓመቱ ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብ ከታቀደው 1.6 ቢሊየን ብር 1.7 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።
እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ በቦንድ ግዢ እና ስጦታ በሀገር ውስጥ 1.2 ቢሊየን ብር፣ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ 95 ሚሊየን ብር፣ ከ8100 ኤ ሰብስክራይበር 123 ሚሊየን ብር እና ከኤሌክትሪክ ኃይል ነጻ የድጋፍ አካውንት የገባ ድጋፍ 212 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ያለምንም የውጭ ዕርዳታም ሆነ ብድር መቶ በመቶ በራስ ዓቅም በመንግስትና ህዝብ የተገነባ ሲሆን፣ መላው ኢትዮጵያዊ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት እና በፐብሊክ ዴፕሎማሲና በአካባቢ ጥበቃ በመረባረብ የተመዘገበው ስኬት በትውልድ የሚዘከር ህያው ድል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በቦንድ ግዢ እና ስጦታ በሀገር ውስጥ ከ20.1 ቢሊየን ብር በላይ፣ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ 1.6 ቢሊየን ብር በላይ፣ ከልዩ ልዩ ገቢዎች 1.7 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ በአጠቃላይ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ከህብረተሰቡ ከ23.6 ቢሊየን ብር በላይ ተሰብስቦ ለግድቡ ግንባታ ውሏል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በአባይ ተፋሰስ ዙሪያም ከ84.4 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የጉልበትና የተፋሰስ ሥራዎች ተሰርቷል፡፡
አሁንም የማጠናቀቂያ ስራዎችን ለማከናወን ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጥሪ አቅርቧል።
በሄለን ጀንበሬ