በክረምቱ አልፎ አልፎ የሚኖር ከባድ ዝናብ ሊያስከትል ከሚችለው ቅጽበታዊ ጎርፍ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ

You are currently viewing በክረምቱ አልፎ አልፎ የሚኖር ከባድ ዝናብ ሊያስከትል ከሚችለው ቅጽበታዊ ጎርፍ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ

AMN ሐምሌ 15/2017

በመጪዎቹ አስር ቀናት አልፎ አልፎ የሚኖረው ከባድ ዝናብ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ እንዳስታወቀው በመጪዎቹ አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በበርካታ ቦታዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ይኖራቸዋል።

በተጨማሪም በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅ እና በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚኖራቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጿል።

የሚጠበቀው እርጥበት ለወቅቱ የግብርና ስራ እንቅሥቃሴ በአመዛኙ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ትንበያው ያሳያል።

ስጋቶችን ለመቀነስና የሚኖሩትን መልካም አጋጣሚዎች በላቀ ሁኔታ ለመጠቀም የቀረቡትን ቦታ ተኮር የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦች በተገቢው ሁኔታ መተግበር እንደሚያስፈልግ አመላክቷል።

በሚኖረው እርጥበት ዘር መዝራት፣ ትርፍ ውሃን ከማሳ በማጠንፈፍ ማስወገድ፣ የአፈር መሸርሸር ስጋትን ለመቀነስ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል።

ረባዳማ በሆኑ ማሳዎች የውሃ ማንጣፈፍ ስራዎች መስራትና የደረሱ የበልግ ሰብሎችን በሚኖሩ ደረቅ ቀናቶች መሰብሰብ እንዲሁም የሚገኘውን እርጥበት በመጠቀም የመኸር ዘር መዝራት እንደሚገባም አብራርቷል።

በቀጣዮቹ አስር ቀናት በሚኖረው ዝናብ በአብዛኛው ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖርም መግለጫው ያመላክታል።

አልፎ አልፎ ከሚኖረው ተደጋጋሚ የሆነ ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ በተለይም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችል አስረድቷል።

ስለሆነም በወንዝ ዳርቻ እንዲሁም ረግረጋማ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውና የሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት አደጋን በመቀነስ መልካም እድሎችን እንዲጠቀሙም አስገንዝቧል።

የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ማዘጋጀት፣ወራጅ ውሃን በእግርም ሆነ በቀላል ተሽከርካሪ ለማቋረጥ አለመሞከር፣ የጎርፍ የፍሳሽ መውረጃ ቦዮችን ማፅዳት፣ የዝናብ ውሃ ማሰባሰብና ማጠራቀም እንደሚገባ አመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review