በከተማዋ የሚገነቡ ህንፃዎችን የታችኛው ወለል ለመኪና ፖርኪንግ እንዲያውሉ የሚያስገድድ ህግን ተላልፈው ከተገኙ 1 ሺህ 280 ህንፃዎች ውስጥ 1 ሺህ 210 በታችኛው የህንፃው ክፍላቸው የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
አንዳንድ የህንጻ ባለቤቶች ህጉን በመተላለፍ ታችኛውን የህንፃ ክፍል ለሱፐርማርኬት ፣ ለሆቴልና ለካፌ እንዲሁም መሰል የተሻለ ትርፍ ለሚያስገኙ አገልግሎቶች ሲያውሉ ቆይተዋል።
በዚህም በህንፃው ስር ሊቆሙ የሚገባቸው መኪኖች አስፋልት ዳር ለመቆም በመገደዳቸው በአካባቢው የትራፊክ መጨናነቅ ሲያጋጥም መቆየቱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኤልያስ ዘርጋ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ ተናግረዋል፡፡
ቀሪ 70 የሚደርሱትን ቀሪ ህንፃዎችም በቀጣይ አመት አገልግሎቱን እንዲሰጡ ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክተዋል ፡፡
ቀደም ሲል አገልግሎት ላይ የነበረው ደንብ ክፍተት እንደነበረው የጠቆሙት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ የነበረውን የህግ ክፍተት በመቅረፍ በ2016 ዓ.ም ደንብ ቁጥር 165/2016 የፖርኪንግ አስተዳደር አዋጅ መውጣቱንና ደንቡ ከወጣ በኋላ ግን ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
ህግን ተላልፈው የፓርኪንግ ቦታውን ለሌላ አገልግሎት ካዋሉ 183 ህንፃ ባለቤቶችም በደንቡ መሰረት ተቀጥተው ከ18.3 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ነው ዋና ስራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡
በሽመልስ ታደሰ