የድንች ሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርስ ፈንገስ ቀድሞ ለአርሶ አደሩ የሚያሳውቅ እና በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የሚታገዝ መተግበሪያ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
መተግበሪያውን በማበልፀግ ላይ የሚገኙት የዌልስ ተመራማሪዎች እንዳስታወቁት ከሆነ በሽታው በግልፅ ለዓይን በሚታይበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ፣ አርሶ አደሮች ችግሩን በስማርት ስልኮቻቸው እንዲለዩ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የአበርስቲዊዝ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ቡድን እንዳስታወቀው፣ በሽታው በዓለማችን 20 በመቶ ለሚሆነው የየድንች ሰብል ውድመት በምክንያትነት ይነሳል፡፡
ውድመቱ በገንዘብ ሲሰላ የ3.5 በሊየን ዩሮ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም የሚያስከትል ነው የተባለው፡፡
አዲሱ መተግበሪያ ወደ ሥራ ሲገባ አርሶ አደሮች ቀድመው የድንች ማሳቸውን ማከም የሚችሉ በመሆኑ ምርታማነታቸውን ከመጨመሩም በላይ ቀደም ሲል አካባቢን በሚጎዱ ፀረ-ተባይ መድሃኒቶች ላይ የነበራቸውን ጥገኝነትም እንደሚቀንስ ነው የሳይንቲስቶቹ ቡድን የገለፀው፡፡
መተግበሪያው የአርሶ አደሩን አስተያየት አክሎ በነባራዊው ዓለም ፍላጎት እና ችግር ላይ ተመስርቶ የተሠራ መሆኑን ያረጋገጡት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኮምፒውተር ሳይንስ መምህሩ ኤዶሬ አክፖኮጅ ናቸው፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ቴክኖሎጂው በሌሎች ሰብሎች ላይ ተገባራዊ የመሆን አቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ድንች በዓለማችን ካሉ ዋና ዋና ሰብሎች በ4ኛ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን፣ ድንችን በስፋት ማምረትም እጅግ እያደገ ለመጣው የህዝብ ቁጥር ጠቃሚ መሆኑ ይታመናል፡፡
በመሆኑም የድንች በሽታ ጉዳይ የግብርና ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ በዩኒቨርሲቲው የባዮሎጂ፣ የአካባቢ እና ገጠር ሳይንስ ተቋም ተመራማሪ አይስዋሪያ ጊሪጃ ገልጸዋል፡፡
በማሬ ቃጦ