ኢንስቲትዩቱ የመንግስትን እና የግል ዘርፉን ተቋማዊ ለውጥ ለማጎልበት አርዓያ መሆን እንደሚገባው አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

You are currently viewing ኢንስቲትዩቱ የመንግስትን እና የግል ዘርፉን ተቋማዊ ለውጥ ለማጎልበት አርዓያ መሆን እንደሚገባው አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

AMN- ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የመንግስትን እና የግል ዘርፉን ተቋማዊ ለውጥና የመፈፀም አቅም ለማጎልበት አርዓያ መሆን እንደሚገባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የኢንስቲትዩቱን የቢሾፍቱ ማሰልጠኛ ማዕከል የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የስልጠና ክፍሎችንና የስልጠና ማዕከሉን የሥራ እንቅስቃሴን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ ለረጅም ዓመታት የመንግስትና የግል ዘርፉን በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ሙያተኞችን አቅም በመገንባት እና በማብቃት ለበርካታ ዓመታት ጉልህ አሻራውን ማሳረፉን አንስተዋል።

የመንግሥት አገልግሎት እና አስተዳደርን ለማሻሻል የተጀመረውን ሪፎርም በመደገፍም የበኩሉን ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ተቋም መሆኑንም ገልጸዋል።

የቢሾፍቱ ማሰልጠኛ ማዕከልም ለበርካታ ተቋማት ስልጠና በመስጠት፣ በማማከር እና በዘርፉ ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኝ፣ ውብ የአረንጓዴ ገጽታና ሰፊ ግቢ እንዳለው ተመልክተናል ነው ያሉት።

የኢንስቲትዩቱ ማሰልጠኛ ማዕከል ከብልፅግና ጉዟችን ጋር አብሮ የሚራመድ ብቻ ሳይሆን የመንግስትን እና የግል ዘርፉን ተቋማዊ ለውጥ እና የመፈፀም አቅም ለማጎልበት አርዓያ መሆን አለበትም ብለዋል።

ሀገራዊ መሻትን ያገናዘቡ፣ በሰልጣኞች ዘንድ እውቀትን፣ ሀሴትን እና የለውጥ ቁጭትን የሚፈጥሩ ምቹ የማሰልጠኛ፣ የሰልጣኞች ማደሪያና የመዝናኛ ክፍሎችን እንዲገነባም አሳስበዋል።

የፌዴራል መንግሥት የሥልጠና ማዕከሉን ለማዘመን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review