የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የተማሪዎችን የፈተና ውጤት ለማሻሻል የመምህራንን አቅም ማሳደግ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ በተለይም የሁለተኛ ደረጃ መምህራን አቅም እንዲሻሻል የክረምት ልዩ የመምህራንና የትምህርት አመራር አካላት የስልጠና መርሃ ግብር በማዘጋጀት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን መምህራን እያሰለጠነ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የዘንድሮው የክረምት ልዩ የመምህራንና የትምህርት አመራር አካላት የስልጠና መርሃ ግብር በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ ውስጥ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ፣ ስልጠናው መምህራን በሚያስተምሩበት የትምህርት አይነትና የማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያግዛል ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የክረምት ልዩ የመምህራንና የትምህርት አመራር አካላት የስልጠና መርሃ ግብር ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 84 ሺህ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን እንደሚሰለጥኑ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ከባለፈው ዓመት የስልጠና ልምዶችን በመውሰድ ስልጠናው የተሳካ እንዲሆን እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ዘመኑን የሚዋጅና በቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል አሰራር በስልጠናው የተካተተ መሆኑን የተናገሩት የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር)፣ መምህራን እራሳቸውን በቴክኖሎጂ ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆየው ስልጠናው፣ በትምህርት ዘርፉ የመምህራንን አቅም በመገንባት ረገድ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ስለመሆኑ ሰልጣኞች ተናግረዋል፡፡
በዝናሽ ሞዲ