AMN-ሐምሌ 17/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አካታች የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነትን ተደራሽ ለማድረግ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል የኮሪደር ልማቱ አንዱ ነው።
በኮሪደር ልማት የተሻለ የተሽከርካሪ መንገዶችን ከመገንባት ባሻገር ሰፋፊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች ተገንብተዋል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንሰፖርት ቢሮም የብስክሌት ትራንስፖርትን በ2018 ዓ.ም በተደራጀ አግባብ ወደ ስራ ለማስገባት በሂደት ላይ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው።
የብስክሌት ትራንስፖርትን አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ መፅደቁን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንሰፖርት ቢሮ የመሰረተ ልማት ዘርፍ ምክትል ሀላፊ አቶ አስመሮም ብርሀኔ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።
የብስክሌት መጋራትና የብስክሌት መስመር አጠቃቀም ደንብ ቁጥር 183/2017 ፀድቆ ስራ ላይ መዋሉም ተመላክቷል።
በደንቡ መሰረት የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚጀመረው በመጀመሪያና በሁለተኛ ዙር በለሙ የብስክሌት መስመሮች ላይ ብቻ መሆኑን ምክትል ሀላፊው ተናግረዋል።
የብስክሌት ትራንስፖርት የማስጀመር ዋና አላማ “የአረንጎዴ ትራንስፖርት” ወይም ሞተር አልባ ትራንስፖርት ለመዲናዋ ተመራጭ በመሆኑ እና ከባቢያዊ የአየር ብክነትን ከመቀነስ አኳያም ወሳኝ የትራንስፖርት አማራጭ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የዜጎችን ጤና ከመጠበቅ አኳያ የብስክሌት ትራንስፖርት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለፁት አቶ አስመሮም፣ ጤናማ የትራንስፖርት አማራጮች ውስጥ ቀዳሚው ነው ብለዋል።
በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት የሚገቡ የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች ለመስራት የሚያስችል የቢዝነስ ሀሳቦችን ለቢሮው ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።

ከእነዚህ ውስጥ የተቀመጠውን መስፈርት ያሟሉ 10 የብስክሌት ኦኘሬተሮች የቅድመ እውቅና ፍቃድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ፍቃድ ካገኙት ኦኘሬተሮች ውስጥ ሦስቱ ብስክሌቶችን ከውጭ ለማስገባት ሂደት ላይ እንደሆኑና በቢሮው በኩልም የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው እንደሆነም ገልፀዋል።
አንድ የብስክሌት ኦኘሬተር ወደ ስራ ማስገባት የሚችለው ዝቅተኛው የብስክሌት መጠን 300 ብስክሌቶች ሲሆኑ ስኩተሮች ደግሞ ከመቶ ማነስ እንደሌለባቸው አብራርተዋል።
ወደ ገበያው የሚገቡ ብስክሌቶች የምርት ዘመናቸው ከሁለት ዓመታት ያልበለጡ መሆን እንደሚጠበቅባቸው እና ከዚያ በላይ እድሜ ያላቸው ብስክሌቶችን ማሰማራት እንደማይቻል ተገልጿል፡
ከዚህ በተጨማሪ የብስክሌት ትራንስፖርት የሚገቡ ኦኘሬተሮች ብስክሌቶቻቸው ላይ ጂፒኤስ፣ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ እና ሌሎች የደህንነት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን መግጠም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ሜዳማ ቦታዎች ከሚነዱ ብስክሌቶች በተጨማሪ ከፍታና ቁልቁለት ያላቸው አከባቢዎች የሚመቹ የኤሌክትሪክ ብስክሌቶች በዘርፉ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ኦኘሬተሮች ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ማለትም እስከ ህዳር 2018 ዓ.ም ድረስ ወደ ስራ ይገባሉ ብለዋል።
የብስክሌት ትራንስፖርት የህዝብ አቅምና መንግስት ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ ያወጣውን ወጪ ታሳቢ ያደረገ ታሪፍ እንደሚወጣም ተገልጿል።
በሔለን ተስፋዬ