በውጭና በሀገር ውስጥ ሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ሃገሪቱን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሚዲያ ካምፔይን በሚያካሄዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሸን እንደሚካሄድ ተገለጸ

You are currently viewing በውጭና በሀገር ውስጥ ሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ሃገሪቱን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሚዲያ ካምፔይን በሚያካሄዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሸን እንደሚካሄድ ተገለጸ

AMN ሐምሌ 17/ 2017 ዓ.ም

በውጭና በሀገር ውስጥ ሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ሃገሪቱን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሚዲያ ካምፔይን በሚያካሄዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሸን እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በቀጣይ ሦስት ወራት በሀገሪቱ የሚካሄዱ ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ሁነቶች ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በተዘጋጀው የፀጥታ ዕቅድ ላይ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሪፐብሊካን ጋርድ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተውጣጡ ስትራቴጂክና ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ውይይት አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ውይይቱን በመሩበት ወቅት በቀጣይ ሀገሪቱ ከሐምሌ እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም የምታስተናግዳቸውን ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ሁነቶች በሰላም እንዲከናወኑ ከእንግዳ አቀባበል ጀምሮ ስምሪቱን በተደራጀ መልኩ መምራትና ማስተባበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ትኩረት ያደረገ እና ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ተከታታይ ጠንካራ ኦፕሬሽን በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያ እንዲሁም በሁሉም መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ አሰሳና ፍተሻ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

በውጭና በሀገር ውስጥ ሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ሀገሪቱን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሚዲያ ካምፔይን በሚያካሄዱት ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሸን በማካሄድ ለሕግ የማቅረብ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በአፅንዖት ተናግረዋል።

ሁሉም የፀጥታ ተቋማት 24/7 ተቀናጅተው በመስራት በተፈጠረው የቴክኖሎጂ አቅምን እና ብቁ የሰው ኃይልን በመጠቀም የተደራጁ ወንጀሎችን መቆጣጠርና ማስቆም እንደሚገባ ማሳሰባቸዉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review