የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በቀጣናው ግጭትን ቀድሞ የመከላከል ዲፕሎማሲ በማጠናከር ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን አበክሮ እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢጋድ የታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት በሴቶች ፣ ሰላም እና ደህንነት አጀንዳዎች ላይ ያዘጋጀው ቀጣናዊ ከፍተኛ የምክክር ፎረም በኬንያ ናይሮቢ መካሄድ ጀምሯል።
ፎረሙ የተዘጋጀው በኢጋድ ዋና አስተባባሪነት እና የጃፓን መንግስት ድጋፍ ነው።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ምክር ቤቱን የአፍሪካ ቀንድ የሞራል ልዕልና መለኪያ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ምክር ቤቱ ለተቀደሰ አላማ የቆሙ፣ ልዩነት የሚያስወግዱ እና የመጻኢ ጊዜ ድልድይን የሚገነቡ ሰዎች ተምሳሌታዊ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢጋድ ከሁለት ዓመት በፊት ባካሄደው 14ኛው መደበኛ ስብስባ ላይ ምክር ቤቱ መቋቋሙን አስታውሰው ዘላቂ ሰላም የሚገነባ ጠንካራ ኃይል ያላቸውን ታዋቂ እና አንጋፋ ግለሰቦች መያዙን አመልክተዋል።

ዋና ፀሐፊው በንግግራቸው በቀጣናው አንብጋቢ ነው ያሏቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በሶማሊያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ያሉ ግጭቶችን ያነሱ ሲሆን ይህ እየተባባሰ ከመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ጋር ተደምሮ ለቀጣናው መንታ ስጋት መሆኑን አመልተዋል።
የታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት ተአማኒ አደራዳሪዎች በመሆን መደበኛው ማዕቀፍ ሊፈታ ያልቻለውን ችግር ባላቸው የካበተ ጥበብ እና ልምድ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
ታዋቂ ግለሰቦች ያላቸው ገለልተኝነት እና ነጻነት በልኬት የሚሰፈር አይደለም ያሉት ዋና ፀሐፊው ይህም ያላቸውን ተቀባይነት የበለጠ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ዋና ፀሐፊው የኢጋድን ቀጣይ ሁለት ቁልፍ ተቋማዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢጋድ አስቀድሞ ግጭትን የመከላከል ዲፕሎማሲ (preventive diplomacy) ልዩ ትኩረት በመስጠት የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ እንደሚያስገባ ጠቁመዋል።
የታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት በኢጋድ የፖሊሲ መዋቅሮች ውስጥ የበለጠ ስር እንዲሰዱ የማድረግ ስራ ይከናወናል ብለዋል።
ይህም ኢጋድን ግጭትን ከመከላከል ስትራቴጂ ወደ ግጭትን ማስቀረት እና የሰላም ቅድመ ግንባታ ስራዎች እንዲሸጋገር ያደርገዋል ያሉት ዋና ፀሐፊው ይህም ግጭትን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የምክር ቤቱ አባላት አንድነት እና የተስፋ ብርሃንን የማስጠበቅ ታላቅ ሞራላዊ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሁላችን በጋራ በመቆም ሰላምን ገንቢ፣ ተስፋን አለምላሚ ጮራ እና የተሻለውን ነገር ሰሪ መሆን ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ዋና ፀሐፊው ኬንያን ጉባኤውን በማዘጋጀቷ፤ የጃፓን መንግስት ደግሞ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በፎረሙ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴት መሪዎች፣ አደራዳሪዎች፣ ታዋቂ የባህል ሰዎች እና ስፖርተኞች የተገኙ ሲሆን ሁሉን አቀፍ የሰላም ግንባታን አስመልክቶ እንደሚወያዩ ኢዜአ ከቀጣናዊ ተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።