በ ኦሮሚያ ክልል የሰፈነውን ሰላም በዘላቂነት አስጠብቆ የየዘርፉ ልማት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ

You are currently viewing በ ኦሮሚያ ክልል የሰፈነውን ሰላም በዘላቂነት አስጠብቆ የየዘርፉ ልማት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ
  • Post category:ልማት

AMN ሐምሌ 18/2017

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሀይሉ አዱኛ፤ ያለፈውን የስራ ዘመን ውጤት በማውሳት በክልሉ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ ዕቅድ አስመልክተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የክልሉ መንግስት የብልጽግና ጉዞውን እውን ለማድረግ ሰፊ ዕቅድ በማዘጋጀት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በክልሉ የሰፈነውን ሰላም በማስጠበቅ ልማትን በዘላቂነት ለማፋጠን ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት ለመስራት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የህግ ማስከበሩ እርምጃ ውጤታማ መሆኑን አንስተው፤ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ባደረጉት ጥሪ መሰረት በርካታ ታጣቂዎች ወደ ሰላም መመለሳቸውን አውስተዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ባለፈው የበጀት ዓመት በተከናወነው የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ሰላም በመስፈኑ ለሁለንተናዊ ልማት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም በክልሉ በዋናነት ትኩረት የተደረገባቸው ሰላምን በማፅናት የግብርና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የወጪ ንግድን ማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትና ሰፊ የስራ ዕድሎችን መፍጠር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም በተለይ በግብርና ዘርፍ በ2017/2018 የመኸር ወቅት 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 368 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።

በበጋ ወቅት ደግሞ 4 ሚሊየን ሄክታር ላይ በስንዴ በማልማት 163 ሚሊየን 600ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመው፤ የክልሉን ግብርና ከዝናብ ጠባቂነት ለማላቀቅ በቆላማ አካባቢ 237 የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።

ከእነዚህም በ2018 በጀት ዓመት ሰፋፊ የሆኑትን ጨምሮ 163 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት መሰጠቱን አመላክተዋል።

በግንባታ ላይ ከሚገኙት 2ሺህ 826 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መካከል 2ሺህ 602 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊየን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግም እንዲሁ።

ክልሉ በበጀት ዓመቱ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር እና 15 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ታቅዷል ነው ያሉት የቢሮ ሀላፊው።

በተጨማሪም ለመስሪያና መሸጫ የሚውሉ 98ሺህ ሄክታር መሬትና 6ሺህ 818 ሼዶች እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።

ክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት 10ሺህ 500 ኢንቨስተሮችን ለመቀበል አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ይህም ለአንድ ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት 2ሺህ 853 የቡኡራ ቦሩ ትምህርት ቤቶች፣ 30ሺህ 444 የመምህራን መኖሪያ ቤቶች፣ 170 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 22 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት መታደቀዱንም አብራርተዋል።

ይህም በመንግስትና በሕዝብ ተሳትፎ እንደሚፈፀም ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው፤ የጤና መድህን ተጠቃሚ አባላትን ቁጥር 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ለማድረስ ይሰራል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ የገቢ ግብርን መሰብሰብ ጨምሮ ሌሎችንም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ተግባራት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጠሉ የቢሮ ኃላፊው ሀይሉ አዱኛ አብራርተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review