“ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ትልቅ አለኝታ ነው”

You are currently viewing “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ትልቅ አለኝታ ነው”

የውሃ ሀብት አስተዳደር አማካሪ አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ

ግድቡ ኢትዮጵያን ከጎረቤትና ከዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚያስተሳስር ገመድ እንደሆነ ተገልጿል

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተበሰረ። የዓባይን ውሃ የመጠቀም የኢትዮጵያ የዘመናት ህልምም ወደ ተግባር ተቀየረ። የግንባታው ሂደት እጥፋቶችን አልፏል፣ ፈተናዎችንም እያስተናገደ ቆይቷል። ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለጉዳዩ በተሰጠው ትኩረት ውሃ መያዝ እና ሀይል ማመንጨት ያስቻሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ የግድቡ ግንባታ ክረምቱ ሲያልቅ በይፋ እንደሚመረቅ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በቅርብ ዓመታት በተለይ እንደአሁኑ የክረምት ወቅት ሲመጣ፣ የግድቡ የውሃ ሙሊት በሚከናወንበት ወቅት ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎች ቀላል እንዳልነበሩ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን ያውቁታል፡፡

አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ አስተዳደር ዳይሬክተር፣ በመቀጠልም የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል፡፡ በግድቡ ድርድር ሂደት ተሳትፈዋል፡፡ የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ዲፕሎማሲ ላይ በአማካሪነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

አቶ ፈቅአህመድ እንደሚገልፁት፣ የግዙፉ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ከፋይናንስ፣ ደህንነት (የአካባቢ ፀጥታ) እንዲሁም ከሁሉም በላይ ከውሃ ፖለቲካው ጋር ተያይዞ ከታችኛው የተፋሰሰ ሀገራት ውስብስብ የሆኑ ፈተናዎች ሲያጋጥሙት ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት የዓባይን ውሃ መጠቀም እንዳትችል ግብፅ በማስፈራራት፣ ብድር እንዳታገኝ በመከላከል፣ አቅሟን አሰባስባ በራሷ እንዳትገነባ በእጁ አዙር ግጭት ውስጥ በማስገባት ጫና ለማሳረፍ ስትሰራ እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት (ሱዳንና ግብፅ) “ጉልህ የሆነ ጉዳት ያስከትላል” በሚል ግድቡ እንዳይገነባ፣ ዲዛይኑ እንዲቀየር፣ የሚይዘው የውሃ መጠን እንዲቀንስ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አቶ ፈቅአህመድ ያነሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር መረጃ ትለዋወጥ ነበር፡፡ የግድቡ ግንባታ ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ የተጀመረ ቢሆንም፤ መተማመንን ለማጎልበት ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ተደርጎ ለአንድ ዓመት የግድቡን ሁኔታ አጥንቷል፡፡ ቡድኑ የሰጣቸውን ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቶ፤ በ2007 ዓ.ም ሦስቱ ሀገራት የመርሆች ስምምነትን ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ ሦስቱ ሀገራት የዓባይን ውሃ ምክንያታዊና ጉልህ ጉዳት አለማድረስ በሚለው መርህ መጠቀምና የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት እና አሰራር በተመለከተ በትብብር እንደሚሰሩ ያመለክታል፡፡

ከመርሆዎች ስምምነት በመነሳት በግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ተከታታይ ድርድሮች እየተካሄዱ ባለበት ወቅት ግብፅ አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት እንዲገቡ ጥያቄ ማቅረቧን አቶ ፈቅአህመድ ያስረዳሉ፡፡

ድርድሩ ላይ እነ አሜሪካ እንዲገቡ የመፈለግ ዋነኛ ዓላማ፤ በጫና የኢትዮጵያን ግድቡን የመሙላት ሂደት ማደናቀፍ፤ ይህ ካልተሳካ ደግሞ ወደተባበሩት መንግስታት ፀጥታው ምክር ቤት ለመሄድ እንደ መንደርደሪያ ድልድይ መጠቀምን በማለም ነበር፡፡ የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግስት በታዛቢነት ከገቡ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ አደራዳሪነት፣ መጨረሻ ላይ ደግሞ ስምምነት በማርቀቅ ኢትዮጵያ እንድትፈርም ጫና ፈጥረው እንደነበር አቶ ፈቅአህመድ ያስታውሳሉ፡፡

የውሃ ሀብት አስተዳደር አማካሪው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የምትገነባው የሀይል ማመንጫ ግድብ ቢሆንም፣ ግብፅ የተለያዩ ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸውን መረጃዎች ታሰራጭ ነበር። “ግድቡ ውሃ ሲሞላ የአስዋን ግድብ ወደ በረሃነት ይለወጣል፤ ሁለት ሚሊዮን አርሶ አደሮቼ በውሃ እጥረት ከእርሻ ስራቸው ተፈናቅለው ይሰደዳሉ፡፡ ሚሊዮኖች ስራአጥ ይሆናሉ፡፡ ግማሾቹ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይሰደዳሉ፤ ሌሎች ደግሞ ስራ አጥ ስለሚሆኑ በሽብርተኝነት መረብ ውስጥ ይወድቃሉ በማለት ከምዕራባዊያን ድጋፍ ለማግኘት ስትንቀሳቀስ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የግድቡ የውሃ ሙሊት ከተከናወነ በኋላ ሲቀርብ የነበረው ስጋትና በተጨባጭ የታየው የተለያየ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት የተሻለ ዝናብ በመጣሉ የህዳሴ ግድብ የሚያስፈልገውን ውሃ ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ እና የታላላቅ ሀይቆች ቀጣና የተሻለ ዝናብ በመኖሩ የአስዋን ግድብ ውሃ ሙሉ ስለሆነ፤ ግብፅ ምዕራባዊያንን ለማስፈራራት የምትጠቀምበት ካርድ ከሽፏል” ይላሉ፤ አቶ ፈቅአህመድ፡፡

የውሃ አስተዳደር አማካሪው እንደሚሉት፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አለቃቀቅ ላይ አስገዳጅ የሆነ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። የዓባይን ውሃ ድርሻ በብቸኝነት ለመጠቀም በፈረንጆች አቆጣጠር በ1929 ግብፅ ከቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ጋር እንዲሁም በ1959 ግብፅና ሱዳን ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ ስምምነቶቹ የወንዙ ምንጭ ሀገርን (ኢትዮጵያን) የበይ ተመልካች ያደረጉ በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያ “አለን” ለሚሉት የውሃ ድርሻ አንድም ጊዜ እውቅና ሰጥታ አታውቅም። በውሃ ሙሊቱና አለቃቀቅ ድርድሩ ለማሳካት የሞከሩትም በተዘዋዋሪ “አለን” ስለሚሉት የውሃ ድርሻ እውቅና ለማግኘት ነው፡፡

ለምሳሌ አሜሪካና የዓለም ባንክ በተሳተፉበት ሲካሄድ በነበረው የሦስቱ ሀገራት ድርድር በውሃ ሙሊቱ ወቅት የወንዙ ፍሰት ከ35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በታች ከሆነ “ኢትዮጵያ ግድቡን አትሞላም” የሚል ሀሳብ ይዘው ቀርበው ነበር፡፡ ይህ ማለት የተጠቀሰው መጠን ያህል ውሃ የእነሱ ድርሻ ነው ብሎ እውቅና መስጠት ማለት እንደሆነ አቶ ፈቅአህመድ ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከግብፅ የሚሰማው ክስ፤ “አለኝ” በምትለው የውሃ ድርሻ ላይ እውቅና ለማግኘት እንጂ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያስፈልገውን ውሃ ይዟል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀጥለው ሀይል የማንጨት ሂደት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመጣውን ውሃ ተቀብሎ የመልቀቅ ጉዳይ በመሆኑ ወደታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚሄደውን የውሃ መጠን አይቀንሰውም ብለዋል፡፡

አቶ ፈቅአህመድ እንደሚገልፁት፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ስታከናውን ታራምድ የነበረው አቋም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ምክንያታዊና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ፣ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ማሳተፍ፣ ግልፅነትን መፍጠር መርሆዎቿ ናቸው። እነዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰራባቸው ተሞክሮዎች ስለሆኑ ማንም ውድቅ ሊያደርጋቸው አይችልም።

ድርድሩ አሜሪካና የዓለም ባንክ ከሚዘውሩበት ሂደት ወጥቶ በአፍሪካ ህብረት መሪነት እንዲያዝ የተደረገበት መንገድ ስልታዊና በሳል ውሳኔ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረት ከአሜሪካና ከዓለም ባንክ በተሻለ የኢትዮጵያን ፍላጎት፤ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ስጋት መረዳት ይችላል፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መምህር አበራ ሄብሶ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ በዲፕሎማሲው አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት እውነት አስፈላጊ ቢሆንም ስራ ይጠይቃል፡፡ የህዝብን አቅም መጠቀም፣ ወዳጅና አጋሮችን ከጎን ማሰለፍ በሚቻልበት ልክ ነው ውጤት የሚገኘው፡፡ በዚህ ረገድ በተለያየ ጊዜያት ኢትዮጵያን ያገለገሉና በማገልገል ላይ ያሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ ምሁራንና ዜጎች እውነታውን በማስገንዘብ ረገድ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል፡፡ በዚህም የግድቡን ግንባታ ስኬታማ በሆነ መልኩ ማከናወን ላይ ቀላል የማይባል አበርክቶ አድርጓል፡፡

የተፋሰሱና ቀጣናው ሀገራት በረከት

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ መያዙ ለሱዳንና ግብፅ እንዲሁም ለቀጣናው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ግድቡ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት እንደ ትልቅ አለኝታ የሚወሰድ የጋራ ሀብት እንደሆነ ፈቅአህመድ ያስረዳሉ፡፡ “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባይኖር ኖሮ፤ አሁን በግድቡ ውስጥ ያለው ውሃ ወደ ሜዴትራኒያን ባህር ገብቶ ይባክን ነበር፡፡ ምክንያቱም የአስዋን ግድብ ሙሉ ነው፡፡ ግድቡ በመገንባቱና ውሃ በመያዙ በላይኛው የአባይ ተፋሰስ ከ70 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ መጠባበቂያ ውሃ አለ፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ትልቅ አለኝታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ውሃ ሀይል እያመነጨ ቀስ በቀስ ሲለቀቅ፤ የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን በጣም ሳይቀንስ እንዲቀጥል ይረዳዋል፡፡”

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ “ግድቡ ለሱዳንና ግብፅ በረከት እንጂ በፍፁም ጉዳት አያመጣባቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልማት፤ የእነሱም ልማት ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው ሀይል ለሁሉም ጎረቤቶች የሚዳረስ ነው፡፡ ወደፊትም ኢትዮጵያ የግብፅ ወንድምና እህት ህዝብን ጉዳት ማየት አትፈልግም፤ ተባብሮ ማደግ ነው የምትፈልገው፡፡ ሀይሉን፣ ውሃውን በጋራ በመጠቀም ልማት እናመጣለን፡፡” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

አቶ ፈቅአህመድ እንደሚገልፁት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከጎረቤትና ከዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚያስተሳስር ገመድ ነው፡፡ ለአብነት ሱዳን በየጊዜው ክምረት በመጣ ቁጥር ከሚያጋጥማት የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ግድቦቿም በደለል ከመሞላት በመታደግ፣ ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ውሃ እንድታገኝ በማስቻል ለልማቷ ትልቅ አለኝታ ይሆናታል፡፡ ሱዳን ከገባችበት የፖለቲካ ችግር ጋር ተያይዞ ወደ ግብፅ የማድላት ሁኔታ የሚታይባት ቢሆንም ወደተረጋጋ ሁኔታ ስትመጣ እውነታውን በመቀበል እንደቀደመው ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም ይጠበቃል፡፡

“The Economic Significance of the Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD) to Eastern Nile Economies” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ2020 ቴዎድሮስ ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) እና ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) በጋራ በሰሩት ጥናት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ስለሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ተብራርቶ ተቀምጧል፡፡ በዚህ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማህበር ባለቤትነት በወጣው የፖሊሲ ጥናት ወረቀት ላይ እንደተመላከተው፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በየዓመቱ በ1 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንዲያስመዘግብ ያደርገዋል፡፡ የሀይል አቅርቦት ማደግ ምርታማነትንና ቅልጥፍናን በማሻሻል የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ ያግዛል፡፡

የሱዳን ኢኮኖሚም በ1 ነጥብ 2 በመቶ እንዲያድግ ምክንያት ይሆናል፡፡ ወደ ግድቦቿ የሚገባውን ደለል በማስቀረት የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎቿ በአግባቡ ሀይል እንዲያመነጩ ያደርጋል፡፡ ግብፅም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ወደ ስራ መግባት በታላቁ አስዋን ግድብ በትነት መልክ ይባክን የነበረውን ውሃ በመቀነስ ወደ ሀገሪቱ የሚደርሰው የውሃ መጠን እንዲጨምርና ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ውሃ እንድታገኝ ያስችላታል፡፡

አቶ ፈቅአህመድ እንደሚገልፁት፤ ሌሎች የዓባይ (ናይል) የተፋሰስ ሀገራትም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተምሳሌትነት በመውሰድ ወደ ልማት እንዲገቡ የሚያበረታታ፣ ሞራላቸውን የሚያነሳሳ፣ አቅጣጫ የሚያመላክት የተፋሰሱ ሐውልት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም (ዶ/ር)፣ “ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት ነው፡፡ ለመላው አፍሪካ መቻልን ያሳየንበት፣ ስንፈትን፣ በውስጣችን ያለውን ውድቀት ጨክነን ወስነን ያረምንበት ነው፡፡ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የያዝንበት፣ ከፍተኛ ሀይል የምናመርትበት ነው፡፡ አፍሪካውያን ብድር ቢከለከሉ፤ የዲፕሎማሲ ጫና ቢደረግባቸው የራሳቸውን ሀብት በገዛ ዜጎቻቸው ማልማትና መቀየር እንደሚችሉ በተግባር የሚያስተምር ስራ ነው” ሲሉ ነበር የገለፁት፡፡ 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2020 ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው 56 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የዘመናዊ ኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ አይደለም፡፡ በርካታ ህዝብ በጨለማ ይኖራል፤ ለምግብ ማብሰያነትም እንጨትን ይጠቀማል፡፡ ግድቡ ኢንዱስትሪዎች እያጋጠማቸው ያለውን የሀይል አቅርቦት እጥረት በመቅረፍ፣ የገጠሩን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ በማድረግ እና የተረፈውን ወደ ውጭ ሀገር በመሸጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ትልቅ የልማት ሀይል ነው፡፡ ሀገሪቱን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት ከተወሰዱ ግዙፍ እርምጃዎች ወይም ግንባታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ህዝብን በማስተባበርና በማስተሳሰር ትልቅ ሚና የተጫወተ፣ የሀገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተለይ ከሀይል ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮችን የሚፈታ ነው፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review