ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተከለቻቸው ችግኞች መካከል 27 ነጥብ 5 በመቶ ያህሉ በአባይ ተፋሰስ መተከላቸውን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ90ሺህ እስከ 100ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ደን ይጨፈጨፍ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ይህ የደን ጭፍጨፋ ድርቅ፣ ጎርፍና የተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት ሲሆን መቆየቱን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮችን ለመቀልበስ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ መከናወን መጀመሩን አስታውሰዋል።
መርሃ ግብሩ ተግባራዊ በተደረገባቸው ባለፉት ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው፤ የተገኘው ውጤት የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን አንስተው ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከተተከሉ ችግኞች መካከል 27 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው በአባይ ተፋሰስ ውስጥ መተከሉንና በዚህም የአባይ ተፋሰስ የእጽዋት ሽፋን ወደ 25 በመቶ ማደጉን አስታውቀዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በመርሃ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞችን ጨምሮ እንደሀገር ለመትከል የተያዘውን የ50 ቢሊዮን ግብ ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
በተያዘው ክረምትም ተጨማሪ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ሀገራዊ ግብ ተይዞ በይፋ ተከላ መጀመሩን ማንሳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአፈር መሸርሸርን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ እንዲሁም ለም አፈር በውሃ እንዳይወሰድ ትልቅ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
ከእርሻ ማሳ ላይ በየዓመቱ 130ቶን አፈር ይሸረሸር እንደነበር ጠቁመው፤ በተሰሩ ሥራዎች የሚሸረሸረውን የአፈር መጠን ከነበረበት ወደ 50 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ከማድረግ ባለፈ ደርቀው የነበሩ የውሃ አካላት መልሰው እንዲጎለብቱ እያገዘ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጨምረው አስታውቀዋል።
ለአብነትም የሀረማያ ሀይቅ መልሶ እንዲያገግም በማድረግ በኩል የአረንጓዴ ዐሻራ ትልቅ አቅም መፍጠሩንም ተናግረዋል።
የአፈር መሸርሸር መቀነሱ ለምርትና ምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው ይህም እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዙ ውጥኖች ግባቸውን እንዲመቱ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የአቮካዶ ምርትን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባሻገር ለውጭ ገበያ እየቀረቡ መሆኑም ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ለአብነት አንስተዋል።