በመዲናዋ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ችግሩን በዛላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

You are currently viewing በመዲናዋ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ችግሩን በዛላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

AMN- ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም

በመዲናዋ 247 ቦታዎች ለጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸው ተለይቶ ችግሩን በዛላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ገለጹ፡፡

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ የ2017 በጀት ዓመት የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን የስራ አፈጻጸም እና የ2018 የትኩረት አቅጣጫን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም በ2017 በጀት ዓመት በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የተሳለጠና የዘመነ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ረገድ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ በዚህም የህዝብን አመኔታ ያተረፉ ተቋማትን መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

ስማርት የመንግስት አስተዳደር ስርአትን በመዘርጋት የተሟላ ደህንነት የሰፈነባት ጽዱና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማን በመፍጠር ረገድ አበረታች ስራ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘመናዊ የቆሻሻ አስተዳደር ስርአትን መፍጠርና ህዝብን ያሳተፈ የመሰረተ ልማት ጥበቃ ስራዎችን ማከናወን የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም በመግለጫቸው ተናግረዋል።

በግንባታ ቦታዎች ያሉ የአደጋ ስጋቶችንና የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥን ማጎልበት ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

እንዲሁም የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና ማስቀጠል ዋነኛ የ2018 የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በመዲናዋ የጎርፍና ተያያዥ የአደጋ ስጋት ተጋላጭነትን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ያነሱት።

በመዲናዋ 247 ቦታዎች ለጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸው ተለይቶ ችግሩን በዛላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ሰሞኑንም በከተማው አንዳደንድ አካባቢዎች በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር የተቻለውም አስቀድሞ በተወሰደው የጎርፍ ማቅለያ ስራዎች ነው ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ከ60 በላይ ትላልቅ የጎርፍ ማፋሰሻ ግንቦች መገንባታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ የሚከናወነው የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችም መዲናዋን የሚመጥን የጎርፍ መከላከልን ባጣጣመ መልኩ እየተከናወኑ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በሔኖክ ዘነበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review