በአዲስ አበባ ከተማ በ2017 በጀት ዓመት ከተጠናቀቁ 28 የጤና ልማት ዘርፍ ፕሮጀክቶች መካከል 22 ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በምረቃ መርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ አዲስ አበባ ከተማን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ መንግስት በጤናው ዘርፍ ከሚያከናውነው ተግባር ጎን ለጎን ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር በመተባበር በርካታ የጤና ዘርፍ ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቦሌ፣ ልደታ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ፕሮጀክቶችን የመረቁት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት 15 ሺህ 960 የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት እያበቃ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ በዛሬው እለት ተጠናቅቀው ለተመረቁ የጤና ልማት ፕሮጀክቶች ብቻ 4 ቢሊየን ብር በጀት ተመድቦ መሠራቱን ገልጸዋል።
የተመረቁት ጤና ጣቢያዎች ለአገልግሎት የሚያስፈልጋቸው መሳሪያ እና የሰው ሀይል ተሟልቶላቸው መመረቃቸውን እና በቀጥታ ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ገልጸዋል።
ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና ጣቢያዎችን ከማስፋፋት ባሻገር ጤና ጣቢያዎቹ የሚሰጡት አገልግሎት በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ደረጃ እንዲሆን ተደርጎ መደራጀቱንም ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስታወቁት።
ከተመረቁት የጤና ፕሮጀክቶች መካከል 9 አዳዲስ የጤና ጣቢያዎች እና 13 የነባር የጤና ጣቢያዎች ማስፋፊያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሁለት ትላልቅ አዳዲስ ሆስፒታሎች እንዲሁም በአራት ነባር ሆስፒታሎች የተሰሩ እና የነባሮቹን ሆስፒታሎች አገልግሎት ከእጥፍ በላይ ያሳድጋሉ የተባሉ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችም በቀጣይ ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ አመላክተዋል።
በሰብስቤ ባዩ