በየዓመቱ ሐምሌ 19 የሚውለው የቁልቢ ገብርኤል ንግሥ ክብረ በዓል በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ዛሬ ተከብሯል።
በዘንድሮው የንግሥ ክብረ በዓል የታደሙ ምዕመናን በፍቅር፣ በመደጋገፍ አብሮነትና አንድነትን በሚያጎላ መንገድ ማክበራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በበዓሉ ላይ ከታደመት መካከል ፤አቶ ቢኒያም ደምወዝ ፤ በዓሉን ምዕመናኑ በሚታወቁበት አብሮነት፣ አንድነትና በመደጋገፍ እሴት አክብረነዋል ብለዋል።
ሌላው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ተስፋዬ ታፈሰ፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጡት ምዕመናን ጋር በዓሉን በጋራና በአብሮነት ማክበራቸውን ተናግረዋል።
በተለይ የጸጥታ አካላትና የአካባቢው ማህበረሰብ በዓሉ ዋዜማ እስከ ፍፃሜው ድረስ ላደረጉላቸው መስተንግዶና እንክብካቤ ምስጋና አቅርበዋል።
ሁላችንም የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴቶቻችንን በማጎልበት የሀገርን ሰላም አስጠብቀን ማስቀጠል አለብን ሲሉ መልዕክት አስተላለፈዋል።
በዓሉን ከመንፈሳዊነቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጎለብት መንገድ ማክበራቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሳራ ፍቃዱ ናቸው።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ አዛዥ እና የበዓሉ አከባበር ግብረ ሃይል ሰብሳቢ ረዳት ኮሚሽነር ናስር መሀመድ እንደተናገሩት፤ በዓሉ ያለምንም የወንጀል ድርጊትና የትራፊክ አደጋ ሳይከሰት በተረጋጋ ሁኔታ ተከብሯል።
ለዚህም የፀጥታ አካላት ጥምረት በመፍጠር ያከናወኑት የተጠናከረ ጥበቃ ስራ አስተዋጽኦ ማድረጉን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብም ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ያከናወኑት ስራ አበረታች መሆኑንም አንስተዋል።