በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የማስፋፊያ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የጤና ተቋማትን መርቀው ከፍተዋል፡፡
በመርሐ-ግብሩም፣ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ በጥራት በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ መደረጉን አንስተዋል።
በተለይ የከተማ አስተዳደሩ የማህበረሰቡን የልማትና የአግልግሎት ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ አቋም ይዞ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ ነዋሪው አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ፣ አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶችን የሚሰጡ ጤና ጣቢያዎች የመገንባት እንዲሁም ማስፋፊያና የማዘመን ስራዎች መስራቱን ገልፀዋል።
ይህም የከተማ አስተዳደሩ ለጤናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን ተናግረዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ፣ በ2017 በጀት ዓመት በጤና ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው የአካባቢው ማህበረሰብ የረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየው የጤና አገልግሎት በአጭር ጊዜ በጥራትና ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማጠናቀቅ ለህብረተሰቡ ምላሽ የሰጠ ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።
ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም፣ ጤና ጣቢያ በአካባቢያቸው መሰራቱ ከተለያዩ እንግልት እና ወጪዎች እንደታደጋቸው ገልፀዋል።
ነዋሪዎቹ አያይዘውም ከተማ አስተዳደሩ ለጤናው ዘርፍ እያደረገ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
በመሀመድኑር ዓሊ