ጊዜው ጠንካራ፣ አካታችና ፍትሀዊ የምግብ ሥርዓትን ለማስፈን የጋራ ጥረት ለማድረግ ሀላፊነት የምንወስድበት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛዉ የተመድ ምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ተናግረዋል፡፡
ምግብ ጤናችን፣ ኢኮኖሚያችንን፣ አካባቢያችንን እና መፃዒውን ዘመናችንን መልክ የሚያስይዝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይሁንና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ፈተናዎች እያጋጠሙት ይገኛል ብለዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግጭት፣ በኢ-ፍትሀዋነት እና በኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት በዓለም ደረጃ የምግብ ሥርዓት ፈተናዎች እንደተጋረጡበት አንስተዋል፡፡
የልማት ድጋፎች እየቀነሱ መምጣታቸውንና ዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፍ ትብብሮችም ውጥረት ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች ምርታማትን፣ አቅርቦትን እና የህዝቦችን ክብር እና ተረጋቶ የመኖር መብት እየተፈታተነ ይገኛልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፡፡
ኢትዮጵያ በምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽ ሥራዋ በምግብ እራስን መቻል ላይ አተኩራ መስራቷንም አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ ሀገራዊ ምርቶች ላይ በስፋት መሰራቱን የገለፁ ሲሆን ይህም ለሀገራችን እና ለህዝባችን መፃዒ ዘመን የሚሆን ጠንካራ ሥርዓት እየገነባን ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽ የሚሆን ግልጽ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታለች፤ ፍኖተ ካርታውም ከማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር የተጣጣመ መሆኑን አስገዝንበዋል፡፡
በተለይም ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ እና ማሻሻል ለምንፈልገው አጠቃለይ የቢዝነስ ሥርዓታችንም ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ግባችን ግልጽ ነው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገብ ማስቻል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ ለስኬቱም ዘርፈ ብዙ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡