ማምረት ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ የምርት ስርጭት ሰንሰለትን መፍጠር እንደሚገባ ተገለፀ

You are currently viewing ማምረት ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ የምርት ስርጭት ሰንሰለትን መፍጠር እንደሚገባ ተገለፀ

AMN – ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም

ማምረት ብቻ ሳይሆን የተመረተውን ምግብ ለገበያ ለማቅረብ አስተማማኝ የሆነ የምርትና ስርጭት ሰንሰለትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ገለፁ።

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በአፍሪካ ሲካሄድ የመጀመሪያ በሆነው የምግብ ስርዓት ጉባኤ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጉባኤዉ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ የተፈለገዉ በምግብ ስርዓት ላይ አፍሪካን ዋና ተዋናይ አድርጎ ማሳተፍ አስፈላጊ ነው ሆኖ በመገኘቱ ነዉ ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ባለፉት 70 ዓመታት የዓለም የምግብ ዋስትና ችግርን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ቢቻልም፤ 10 በመቶ የሚሆነዉ የአለም ህዝብ አሁንም ድረስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለመቻሉን እና አብዛኛው ችግር በአፍሪካ እንደሚስተዋል ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ከ 5 ሰዎች አንዱ ለረሃብ የተጋለጠ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስተሯ ጤናማ ኑሮን ለመኖር የሚያስችል የተመጣጠነ ምግብ እንደማያገኙም ተናግረዋል።

ወረርሽኞችን ጨምሮ ዓለምን እያጋጠሟት ባሉ ቀውሶች ምክንያት ችግሩ ይበልጥ መባባሱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ በጦርነት ምክንያት የኢኮኖሚ እና ንግድ ፍሰቶች መረበሻቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህም ምክንያት በግብይት ሰንሰለቱ ላይ መሰናከሎች ተፈጥረዋል በተለይም በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም ደቡብ ክፍል የዋጋ ንረትን ፈጥሯል ብለዋል።

ማህበረሰቡ በቂ ምግብ እንዲያመርት ማገዝ ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ የተመረተውን ምግብ ለገበያ ለማቅረብ አስተማማኝ የሆነ የምርት ስርጭት ሰንሰለትን መፍጠርም ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህም ማህበረሰቡ ያለዉን የተፈጥሮ ሃብት መጠቀም፣ የስራ እድሎችን መፍጠር እና የተረጋጋ ዘላቂ እድገት እንዲኖር ለማድረግ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review