አስደማሚው ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማድረግ ጉዞ ከተጀመረ እነሆ 7 ስኬታማ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ያማረ ሀገርን ለትውልድ የማስተላለፍ አካል የሆነው ይህ ታላቅ መርሀግብር በመሪዋ አርአያነት የተሞላው ተግንባር እየተመራ እና በህዝብ የነቃ ተሳትፎ የዓለምን ቀልብ የገዛ ሥራ ማከናወን የተቻለበት ሆኗል፡፡
ለተከታታይ ዓመታት በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሀግብርም ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡

በነዚህ ዓመታት የተተከሉት ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡት ችግኞች ትርጉም ያለው ውጤት እያመጡ ይገኛል፡፡
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በተካሄደው በ2ኛው የተመድ የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ከናይጄሪያ የመጡት ሳጆ ፋኒያ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በስፋት እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ ችግኝ ተከላ መርሀግብር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የጀመረችው ጉዞ እንደሚሳካ አመላካች ይሆናል ብለዋል፡፡
በርካታ የዛፍ ዝርያዎች እየተተከሉ መሆናቸው አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል ሲሆን፣ ምርትና ምርታማትን ለመጨርም አይነተኛ መንገድ ነው ያሉት ደግሞ ከአየርላንድ የመጡት ቻርም አርኖልድ ናቸው፡፡
ከአፍሪካ ሀገር በቀል ምርቶች አቅራቢ ድርጅት የተገኙት ሰሚራ ሀጁባጀሪ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የተራቆቱ መሬቶችን ችግኝ በመትከል እንዲያገግሙ ማድረጓ በምግብ እራስን ለመቻል አጋዥ እንደሆነና፣ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናን እየተጫወተች ትገኛለች ብለዋል፡፡

አፍሪካ እና መላው ዓለም ከዚህ ልምድና ትምህርት ሊወስድ ይገባል ያሉት የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ መርሀግብር መቀላቀል እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
ይህ የውድድር ጉዳይ ሳይሆን በጋራ መሥራትን የሚጠይቅ ትልቅ ለውጥ አምጪ ተግባር መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
አፍሪካ እና መላው ዓለምም ከዚህ ትምህርት መውሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በማሬ ቃጦ