በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት ሰፋፊ ግድቦችን በመገንባት ከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጠቀሜታዎችን አግኝተዋል። እነዚህ ግዙፍ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ለኃይል ማመንጫ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለጎርፍ መከላከልና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በዚህ ጽሑፍም ትልልቅ ግድቦችን ገንብተው የተጠቀሙ አንዳንድ ሀገሮችን እንመለከታለን።
በጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ ጠንካራ ኢኮኖሚ ወደገነባችውና በርካታ ግድቦች ወዳሏት ቻይና ስናቀና ‘ሦስቱ ገደሎች’ ግድብን እናገኛለን። በዓለም ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሆነው ‘ስሪ ጎርጅ’ ግድብ (Three Gorges Dam) በያንግትዜ ወንዝ ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ለቻይና ከፍተኛ መጠን ያለው ንጹህ ኃይል ያቀርባል። በተጨማሪም ለጎርፍ መቆጣጠሪያነት፣ ለመርከብ ትራንስፖርት እና ለመስኖ ልማት ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል።
ግንባታው እ.ኤ.አ በ2008 የተጠናቀቀው ይህ ግድብ 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በቻይና በያንግዜን ወንዝ ጠባብ ሸለቆዎች ላይ ከተገነቡ ሶስት ግድቦች መካከል 22 ነጥብ 5 ጊጋ ዋት በማመንጨት ‘ሦስቱ ገደሎች’ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከዓለማችን ትልልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጎራ መሰለፍ ችሏል፡፡ በቻይና ‘ስሪ ጎጅስ ኮርፖሬሽን’ የተገነባው ይህ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ቁመቱ 185 ሜትር ሲሆን፣ 2 ሺህ 309 ሜትር ደግሞ ይሰፋል፡፡ ግድቡ በአጠቃላይ ካሉት 32 የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች መካከል በግራ በኩል 14 እንዲሁም በቀኝ በኩል ደግሞ 12 ዋና የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች አሉት፡፡
እነዚህ ኃይል አመንጪ ተርባይኖች እ.ኤ.አ በ2008 ወደ ስራ ሲገቡ 18 ሺህ 300 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ችለዋል፡፡ በኋላ ደግሞ 6 የምድር ኃይል ማመንጫዎች ምድር ውስጥ በሚገኘው የግንባታው ክፍል ውስጥ የተተከሉ ሲሆን፣ ሶስት ዓመታትን ቆይቶ እ.ኤ.አ በ2011 ከእነዚህ 6 ተርባይኖች መካከል ሶስቱ ስራ እንዲጀምሩ ተደረገ። በመቀጠልም በዚያኑ ዓመት ቀሪዎቹ በመሬት ውስጥ የተተከሉት 31ኛ እና 32ኛ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ጀመሩ። በመጨረሻም 32ቱ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ኃይል ማምረት ሲጀምሩ አጠቃላይ ያመነጩት ኃይል 22 ሺህ 500 ሜጋ ዋት ሆኖ ተመዝግቧል ይላል የፓወር ቴክኖሎጂ ዶት ኮም ገፀ ድር መረጃ፡፡
ይህን ግድብ ቻይና በምትገነባበት ወቅት፣ “እኛ እያለን ብቻሽን ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት አትገነቢም፤ ባይሆን በምንችለው ቤት ባፈራው አቅም ሁሉ አለንልሽ” ሲሉ እንደ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ጃፓን እጃቸውን ለድጋፍ እንደዘረጉላት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
አህጉረ አፍሪካም ለረዥም ጊዜ የኃይል አቅርቦት እና የውሃ እጥረት ፈተናዎች ሲገጥሟት ቆይቷል። ይሁን እንጂ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ትልልቅ ግድቦችን በመገንባት እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍና የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። እነዚህ ግዙፍ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለጎርፍ መከላከል እና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ወሳኝ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ለሀገሪቱ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ የሚገኘውና በደቡብ አፍሪካ ያለው ትልቁ የውሃ ማጠራቀሚያ የሆነው ጋሪየፕ ግድብ (Gariep Dam) አንዱ ነው፡፡
ይህ ግድብ በኦሬንጅ ወንዝ ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ለደቡብ አፍሪካ በርካታ ጥቅሞችን ያስገኛል። ከግድቡ ዋነኞቹ ጥቅሞች አንዱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መሆኑ ነው። በግድቡ ግድግዳ ውስጥ የሚገኙት አራት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ጄኔሬተሮች ለደቡብ አፍሪካ የኃይል አቅርቦት ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታሉ። እነዚህ ጄኔሬተሮች በተለይም የኃይል ፍላጎት በሚጨምርባቸው ሰዓታት (peak hours) እና ድንገተኛ ሁኔታዎች ላይ ለሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

ካሪባ ግድብ ላይ ጥናት ያደረጉት አንትሮፖሎጂስቱ ታየር ስካደር እንደሚሉት ግድቡ ከሚያስገኛቸው ትልልቅ ጥቅሞች አንዱ ለመስኖ ልማት የሚያቀርበው ውሃ ነው። ከግድቡ በስተጀርባ ያለው ሰፊ የውሃ ማጠራቀሚያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሄክታር የእርሻ መሬቶች የመስኖ ውሃ ያቀርባል። በተለይም በ‘ኦሬንጅና ፊሽ’ ወንዞች ሸለቆዎች የሚገኙ የእርሻ መሬቶች በጋሪየፕ ግድብ ከሚገኘው ውሃ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ የመስኖ ልማት የሀገሪቱን የምግብ ምርት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይረዳል። ውሃው ወደ ታላቁ ፊሽ ወንዝ በ82 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው ‘ኦሬንጅና ፊሽ’ ዋሻ አማካኝነት ይተላለፋል፤ ይህም ለምስራቅ ኬፕ ግዛት ሰፊ የግብርና አካባቢዎች ውሃ ያደርሳል።
የጋሪየፕ ግድብ ለደቡብ አፍሪካ ከተሞች እና ለኢንዱስትሪዎችም የመጠጥ ውሃ ያቀርባል። እንደ ብሎምፎንቴይን (Bloemfontein) እና ግቄበርሃ (የቀድሞዋ ፖርት ኤልዛቤት) ላሉ ከተሞች የውሃ አቅርቦት ወሳኝ ነው። ይህም የህዝብ ጤናን ከመደገፍ ባሻገር የከተሞችን መስፋፋትና የኢንዱስትሪዎችን ሥራ ያረጋግጣል።
የ‘ሃይድሮ ፓወር ኦርግ’ን ገፀ ድር መረጃን ዋቢ አድርገን ስንመለከት ‘ኦሬንጅና ፊሽ’ ወንዝ ዋሻ በተፈጥሮው በጎርፍና በድርቅ ሁኔታዎች መካከል የሚለዋወጥ ነው። ጋሪየፕ ግድብ የዚህን ወንዝ ፍሰት በመቆጣጠር ለታችኛው የ‘ኦሬንጅና ፊሽ’ ወንዝ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ይረዳል። በዚህም የጎርፍ መቆጣጠሪያ ዘዴ ንብረትን ከመጠበቅ ባሻገር የህዝብን ደህንነት ያረጋግጣል።
ከላይ ከተጠቀሱት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በተጨማሪ፣ የጋሪየፕ ግድብ በአካባቢው ለመዝናኛና ለቱሪዝም ትልቅ አስተዋጽዖ አለው። ግድቡ ያለው ሰፊ የውሃ አካል ለጀልባ ጉዞ፣ ለዓሳ ማጥመድና ለውሃ ስፖርቶች ምቹ ነው። በአካባቢው የሚገኙ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎችም ለቱሪስቶች መስህብ ናቸው። ይህ ደግሞ በአካባቢው የቱሪዝም ኢንዱስትሪን በማሳደግ የስራ ዕድሎችን ይፈጥራል። በአጠቃላይ እንደ ሃይድሮ ፓወር ኦርግ ገፀ ድር፣ የደቡብ አፍሪካው ጋሪየፕ ግድብ ለሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት፣ የምግብ ዋስትና፣ የውሃ አቅርቦትና የጎርፍ መከላከል ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጋሪየፕ ግድብ ለዓሣ አጥማጆች በጣም ተወዳጅ ከሆኑት ስፍራዎች አንዱ ነው። ብዙ ሰዎች ወደዚህ ግድብ የሚመጡት እንደ ካርፕ፣ ባርበል፣ ቢጫ ዓሣ እና ሙድፊሽ ያሉ ዓሳዎችን ለማጥመድ ነው። ግድቡ ለአካባቢው ማህበረሰብም በተለይም ለዓሳ አጥማጆች አስፈላጊ የምግብ እና የገቢ ምንጭ ነው። በአካባቢው ይህ ዓሳ አጥማጅነት በተለይ ሌሎች የገቢ ምንጮች በሚገደቡበት ጊዜ እንደ የደህንነት መረብ ሆኖ ያገለግላል። ጋሪየፕ ግድብ የተረጋጋና ትልቅ የውሃ አካል በመሆኑ ለአንዳንድ የዓሣ ዝርያዎች የተረጋጋ መኖሪያ ይሰጣል።
በዛምቤዚ ወንዝ ላይ የሚገኘው ‘ካቦራ ባሳ’ ግድብም የአፍሪካ ትልልቅ ግድቦች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው። ግድቡ በዛምቢያና በዚምባብዌ መካከል የጋራ ፕሮጀክት ሲሆን፣ በአፍሪካ ከሚገኙት ግዙፍ የውሃ ኃይል ማመንጫዎች አንዱ ነው። ይህ ግድብ ለሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል። የ‘ካቦራ ባሳ’ ግድብ የተገነባው እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ ሲሆን፣ ከግንባታው ወዲህ ለሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚ እድገትና ለብዙ ማህበረሰቦች ብርሃን በመሆን ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ይህ ግድብ በዋናነት ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚያገለግል ሲሆን፣ ለሞዛምቢክና ለጎረቤት ሀገራት የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው። 2 ሺህ 70 ሜጋዋት ኃይል የሚያመነጨው የ‘ካቦራ ባሳ’ ግድብ የሞዛምቢክን ኢኮኖሚ በመደገፍና የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማጎልበት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ወደ አውሮፓ አምርተን በሩሲያ በሳያኖጎርስክ ካካሲያ በዬኒሴይ ወንዝ ላይ የሚገኘውን ‘ሳያኖ-ሹሺንስካያ’ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን በአጭሩ ቃኝተን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡ የኃይል ማመንጫው ግንባታ እ.ኤ.አ በ1963 ተጀምሮ እ.ኤ.አ በ1978 የተጠናቀቀ ሲሆን፣ 10 ኃይል ማመንጫ ክፍሎችን ይዟል፡፡ እነዚህ ማመንጫዎች እያንዳንዳቸው 640 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አላቸው። ‘ሳያኖ-ሹሺንስካያ’ ከሚያመነጨው ኃይል 70 በመቶው በሳይቤሪያ የሚገኙ 5 የአልሙኒየም ማቅለጫ ፋብሪካዎች ይጠቀሙታል፡፡
በመስከረም ሊሞሸር ቀጠሮ የተያዘለትና ኢትዮጵያ የገነባችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የኃይል ፍላጎቷን ለማሟላትና ልማቷን ለማፋጠን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ይሆናል፡፡ ይህ ግድብ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት፣ ለኃይል አቅርቦትና ለቀጠናዊ ትብብር ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ