“የምንተክለው ምግባችንንም ጭምር ነው”

You are currently viewing “የምንተክለው ምግባችንንም ጭምር ነው”

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤ

የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም አሁናዊ ፈተና ነው፡፡ ችግሩ እያስከተለ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን እውን ለማድረግ የደን ልማት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ይህንኑ ባገናዘበ መልኩ ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የአረንጓዴ ልማት መርሐ ግብርን ስታከናውን ቆይታለች፡፡

በኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አዲስ አበባም በመከተል እና ልዩ ትኩረት በመስጠት ላለፉት 6 ተከታታይ ዓመታት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል ችላለች፡፡ ዘንድሮም ለ7ኛ ጊዜ እያከናወነች ባለችው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተጨማሪ ውጤት የሚያስገኝ የተጠናከረ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የመዲናዋን የ2017 ዓ.ም የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብርን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፣ ላለፉት 6 ተከታታይ ዓመታት የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የከተማዋን የደን ሽፋን አሳድጎታል፡፡

ከንቲባ አዳነች አክለውም፣ “የአረንጓዴ አሻራው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መሆን እንዲችል የሚያደርግ ፅኑ መሰረት የተጣለበት ነው፡፡ የምንተክለው ምግባችንንም ጭምር ነው” ብለዋል፡፡

ችግኝ መትከል የምግብ ሉዓላዊነትን የምናረጋገጥበት ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ “የምንተክለው ጥላ ብቻ አይደለም፣ ውበት ብቻ አይደለም፣ ለጫካ የሚሆኑ ዛፎች ብቻም አይደለም፤ የምንተክለው ምግባችንንም በመሆኑ የምግብ ዋስትናችንንም የምናረጋግጥበት ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በእርግጥም ከንቲባ አዳነች እንደገለፁት ችግኞችን መትከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የማይበገር የአየር ንብረት ለውጥን ለመገንባት ወሳኝ ነው፡፡ የዓለም አግሮፎረስተሪን ማዕከል (ICRAF) መረጃም  ይህንኑ ነው የሚያመላክተው፤ በአፍሪካ ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶችን እና ጥናቶችን የሚያካሂደው የአግሮፎረስትሪ ምርምር ማዕከል የዛፍ ተከላ በምግብ ዋስትና ላይ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ሰፊ ስራዎችን ያከናውናል። ዛፎች ካርቦን ዳይኦክሳይድን በመምጠጥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ይረዳሉ። የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ በግብርና ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር፣ የዛፍ ተከላ ቀጥተኛ ያልሆነ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ፋይዳ አለው።

የዓለም አግሮፎረስተሪን ማዕከል (ICRAF) ተመራማሪ የሆኑት ፈርጉስ ሲንክሌርም (ዶ/ር) ችግኝ መትከል ለምግብ ዋስትና ወሳኝ እንደሆነ ይስማማሉ። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም፣ የሰብል ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር፣ የአመጋገብ ጥራትን ያሻሽላል፣ የገቢ ምንጭ ይፈጥራል፣ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ይጨምራል። ይህ ደግሞ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

የቀድሞው የዓለም አግሮፎረስተሪ ዋና ዳይሬክተር ቶኒ ሲሞንስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዛፎች የአፈር መሸርሸርን ይከላከላሉ፤ የአፈርን ለምነት ይጨምራሉ፤ የውሃ አያያዝን ያሻሽላሉ። ይህም የሰብል ምርትን ከፍ ያደርጋል፤ በተለይ ደግሞ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ዛፎች የከርሰ ምድር ውሃን በመሙላት እና የአፈርን እርጥበት በመጠበቅ የሰብል እድገትን ይደግፋሉ።

የፍራፍሬ ዛፎችን፣ ለውዝ የሚያፈሩ ዛፎችን እና ሌሎች የሚበሉ የዛፍ ምርቶችን መትከል የምግብ ምንጮችን በማብዛት የአመጋገብ ዋስትናን ያረጋግጣል። ይህ በተለይ በአንድ የሰብል አይነት ላይ ጥገኛ የሆኑ ማህበረሰቦች የምግብ እጥረትን እንዲቋቋሙ ይረዳል ይላሉ ቶኒ ሲሞንስ (ዶ/ር)።

አክለውም ብዙ ዛፎች እንደ ፍራፍሬ፣ ቅጠላማ አትክልቶች፣ ለውዝ እና የመሳሰሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ምርቶችን ያቀርባሉ። እነዚህም የአመጋገብ ጥራትን በማሻሻል የምግብ እጥረትን ለመቀነስ ይረዳሉ። በተለይም በገጠር አካባቢዎች ለህጻናት እና ለሴቶች የአመጋገብ ደህንነት ወሳኝ ስለመሆናቸውም ያብራራሉ።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳች አቤቤም የአንድነትና የጋራ መንፈስ እየታየበት ያለውና ማህበረሰቡ በጋራ ተስማምቶ ከሰራቸው ትላልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ የሆነው አረንጓዴ አሻራ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በግንፍሌ ቀበና ወንዝ ዳርቻ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፣ መላው ኢትዮጵያውያን ባለፉት 6 ዓመታት በተተከሉ ችግኞች ታላቅ ገድል ሰርቷል፡፡

ከንቲባዋ አክለውም፣ “ችግኝ በመትከላችን በብዙ ተጠቅመናል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ጥብቅ በሆነ መንገድ ያለ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ብሔር፣ ኃይማኖት እና ፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የተተከለው ትልቅ አሻራ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ማብራሪያ መሠረት፣ በአዲስ አበባ በአንድ ጀንበር መርሐ ግብሩ ከ271 ሳይቶች በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በክረምት መርሐ ግብር 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ዓመቱን ሙሉ ችግኞች እንደሚተከሉና በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም 5 ሚሊዮን ችግኞች ስለመተከላቸው ተመላክቷል፡፡ ከ6 ዓመት በፊት የመዲናዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከ2 ነጥብ 8 በመቶ ያነሰ ነበር፡፡ አሁን ላይ 22 በመቶ ደርሷል፡፡ በዓለም አቀፍ መመዘኛ መስፈርት መሰረት ደግሞ ከተሞች 30 በመቶ መድረስ ይገባቸዋል። ይህንን ግብ በ2018 ዓ.ም ለማሳካት እየተሰራ ነው፡፡

አዲስ አበባን በአረንጓዴ ልማት ለማበልፀግ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ውብ፣ ከአፍሪካ እህት ከተሞች መካከል ቀዳሚና ተመራጭ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ይህን ግብ ለማሳካት እንዲቻል የአረንጓዴ ልማት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በመርሐ ግብሩ በ2011 ዓ.ም በመዲናዋ 6 ሚሊዮን 84 ሺህ 372 ችግኞችን መትከል፣ በ2012 ዓ.ም 8 ሚሊዮን 513 ሺህ 531 ችግኞች፣ በ2013 ዓ.ም 11 ሚሊዮን 441 ሺህ 961 ችግኞች፣ በ2014 ዓ.ም 14 ሚሊዮን 795 ሺህ 595 ችግኞች፣ በ2015 ዓ.ም ደግሞ 17 ሚሊዮን 445 ሺህ 385 ችግኞች፣ በ2016 ዓ.ም ደግሞ ከ27 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል እንደተቻለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

በእነዚህ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሚባል ደረጃ የተሳተፉ ሲሆን፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎችም በጋራ ስለ መዲናዋ ገጽታ ግንባታ እና ለጋራ ጥቅም በጋራ መቆምን ለዓለም ያሳዩበት አኩሪ ተግባር ሆኗል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አዲስ አበባ ለጀመረችው የዘመናዊ ከተማ ግንባታ ሂደት አንዱ ገጽታ ሆኖ እየተተገበረም ይገኛል፡፡ ይህ ተግባር ከተማዋን አረንጓዴ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን እየተሰራ ከሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው።

በመሆኑም በየኮሪደሩ በተዘጋጁ የአረንጓዴ እና የመዝናኛ ስፍራዎች ላይ ለመዲናዋ ውበት እና ድምቀት የሚሰጡ የተለያዩ የዕፅዋት አይነቶች በመተከል ላይ ናቸው፡፡ በመዲናዋ የሚገኙ በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎችን ማልማት የተቻለ ሲሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ በስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተሰፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተውበታል፡፡

በተለይ በመዲናዋ እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት እየተተከሉ የሚገኙ ችግኞች የመዲናዋን ውበትና ገጽታ ከማላበስ ባለፈ ጤናማ፣ በአካል ብቃት የዳበረ እና በመንፈስ የተረጋጋ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የላቀ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review