በበጀት ዓመቱ ህጎችን የማውጣት፣ የማሻሻል ብሎም የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በመስራት የህዝብን ጥያቄ ለመመለስና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተኬደው ርቀት ስኬታማ እንደነበር የአዲስ አበባ ምክር ቤት አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2018 የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር፣ በከተማዋ የሚከናወኑ ተግባራት በአግባቡ ይሰሩ ዘንድ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች መደረጋቸውን ገልፀዋል።
ክትትልና ቁጥጥር ሲደረግ ጥያቄ ያለባቸውና በጊዜ ያልተከናወኑ ስራዎች ግብረ መልስ ወዲያው በመስጠት ምላሽ እንዲያገኙ መደረጉንም ወ/ሮ ቡዜና አመላክተዋል።
አለፍ ሲልም በቀጥታ የህዝብ ለህዝብ ውይይት መድረክ በመፍጠር ምላሽ እንዲያገኙ የተደረገበት አግባብ እንደነበርም አብራርተዋል።
የህዝብ ጥቅም ለማስከበርና የህዝብ ውግንና እንዲኖር ለማድረግ የተኬደበት ርቀት የተሻለ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ከህብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በየወረዳው እና በየክፍለ ከተማው እንዲመለሱ ተደርገዋል ያሉት አፈ ጉባኤዋ፣ ከዚያ ያለፈውም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ምላሽ እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል።
የሚሰሩ ስራዎችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ሪፎርም የተደረገበት ዓመት ነበርም ብለዋል።
በከተማዋ የሚሰሩ የልማት ስራዎች በአግባቡ በተባለላቸው ጊዜ ይሰሩ ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ የአስፈጻሚ አካላትን ምዘና አካሂደናል ብለዋል።
ካለፈው ዓመት የወሰድናቸውን መልካም ልምዶች በማስፋት የሕግ አወጣጥ፣ የአስፈጻሚ አካላት ክትትልና ቁጥጥር፣ የመራጭና ተመራጭ ትስስር የውክልና ሥራዎች በልህቀት ለመፈጸምም በ2018 በጀት ዓመት ይሰራል ብለዋል።
ምክር ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።
በሔለን ጀንበሬ