የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለማዕድን ዘርፉ ዕድገት ማስፈንጠሪያ ሆኖ አገልግሏል

You are currently viewing የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለማዕድን ዘርፉ ዕድገት ማስፈንጠሪያ ሆኖ አገልግሏል

AMN- ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ለማዕድን ዘርፉ ዕድገት ማስፈንጠሪያ ሆኖ ማገልገሉን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ብትሆንም በየዘመናቱ የነበሩ መንግሥታት ትኩረት ማነስ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓት ቆይቷል ብለዋል፡፡

ነገር ግን የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ እምርታ እንዲያስመዘግብ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረበው ወርቅ አራት ቶን ብቻ እንደነበር አስታውሰው መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በ2017 በጀት ዓመት ወደ 37 ቶን በማሳደግ 3.5 ቢሊየን ዶላር ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ የጋዝ ምርት ለገበያ እንደምታቀርብ እና ከናይጄሪያው ባለሃብት አሊኮን ዳንጎቴ ጋር በመነጋገር የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት እንደምትጀምር ገልጸዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ፣ በ2017 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ አፈጻጸም መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ገቢራዊ ያደረገችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ከወርቅ ምርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከማሳደግ ጀምሮ የማዕድን ዘርፉ ዕድገት ማስፈንጠሪያ ሆኖ ማገልገሉን ተናግረዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ብቻ ሳይሆን ተኪ ምርቶችን ጭምር በማበረታታት ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘርፉ ላስመዘገበችው ስኬት ከዘርፉ ተዋንያን ጋር የነበራት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ሚናው የጎላ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስመጣት እስከ 300 ሚሊዬን ዶላር ያስፈልጋት እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የድንጋይ ከሰል አቅርቦት እጥረት በመከሰቱ ሲሚንቶ ማምረትና ለገበያ ማቅረብ አስቸጋሪ ነበር ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በ2017 አራት የድንጋይ ማጠቢያ ፋብሪካዎችን በማስመረቅ የሲሚንቶ ምርትን አቅርቦት ማሳደግና ዋጋውን መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ የመጀመሪያውን ምዕራፍ የጋዝ ምርት ለገበያ እንደምታቀርብ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚ ጥቅም እንዲውል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር ድፍድፍ ዘይትን ጨምሮ ያልተጠቀምንባቸው የማዕድን ሀብቶች እንዳሉ ገልጸው፣ የማዕድን ሀብቶችን ለሀገር ጥቅም ማዋል ይገባል ብለዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ኢንጂነር ሀብታሙ፤ ሀገራችን ያላትን ሰፊ እና ለም የእርሻ መሬት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ጋዝ ማውጣት ከሽያጭ ባለፈ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለውን የዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል አቅም መፍጠር ጭምር መሆኑንም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚሀም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል የተግባር እንቅስቃሴ መጀመሯንም አስታውሰዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review