የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑን ከሚረጋገጥባቸው ስራዎች መካከል የኮሪደር ልማቱ በተጨባጭ ማሳያ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ።
የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት አዲሱን እና ከእንጦጦ እስከ አራት ኪሎ ፕላዛ ተገንብቶ የተመረቀውን የኮሪደር ልማት ተመልክተዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው ለአፍሪካም ሆነ ለታዳጊ ሀገራት የከተማ ልማት አመራር ስታንዳርድ ስርዓት ምሳሌ ብሎም የፓርቲው መፍጠንና መፍጠር መርህ በተግባር የተረጋገጠበት ስራ መሆኑን አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል።
ብልፅግና ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚመጥን መልኩ ማሰብ፣ማቀድ፣ሁሉንም አቅም አስተባብሮ ስራን በጥራትና በግዜ በማጠናቀቅ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚችል በኮሪደር ስራ የገለጠበት መሆኑንም ጭምር አብራርተዋል።
ከተሞች ለሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ያላቸው ፋይዳም የታየበት ይህ ስራ የአመራሩ ቁርጠኝነትና ቃል በተግባር የተረጋገጠበት ብሎም የባለሙያውን እውቀትና ክህሎት በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያሳየ ስራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ለስራው ስኬታማነት ህዝቡ ከስራው ጅማሮ አንስቶ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ከማህበራዊ ልማቱ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ይገኛልም ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የከተሞችን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ወጣቶችም ኢኮኖሚው በፈጠረው የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ያብራሩት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ስራው በሌሎች አካባቢዎችም በስፋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሥራው ስኬታማ እና ያማረ እንዲሆን ላስቻሉ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ላቅ ያለ ምስጋናም አቅርበዋል።
በሚካኤል ህሩይ