አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በበጀት ዓመቱ በተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች የተሸለ አፈፃጸም ያስመዘገቡ ሰራተኞችን የሚያበረታታ የዕውቅና ሳምንት አካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት የላቀ አፈፃጸም ላስመዘገቡ ተቋማት ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕውቅና በሰጠበት መርሐ-ግብር ልዩ ተሸላሚ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ በበጀት ዓመቱ የላቀ አፈፃጸም ያሳዩ የተቋሙ ሰራተኞችን ለማበረታታት ዓላማ ያደረገ የእውቅና ሳምንት አካሂዷል፡፡
ከሐምሌ 21 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው የዕውቅና ሳምንት፣ በተቋሙ ባሉ የተለያዩ ዘርፎች የላቀ አፈፃጸም ያስመዘገቡ ሰራተኞች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፣ ዕውቅናው የተሸለ አፈፃጸም ያስመዘገቡ ሰራተኞች እንዲበረታቱ እና ሌሎችም በቀጣይ የተሸለ አፈፃጸም ለማስመዝገብ እንዲጥሩ ማነሳሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ሰራተኞች በትጋት እየሰሩ እንደሚገኙ እና ተቋሙ ለሽልማት እንዲበቃ የየበኩላቸውን አስተዋፅዖ አድርገዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ሁሉም ተሸላሚ እንደሆኑ አንስተዋል፡፡
ይሁንና በዓመቱ በየዘርፉ ተመዝነው የላቀ አፈፃጸም ያስመዘገቡ ሰራተኞች ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልጸው፣ ማበረታቻው ሁሉም ለመሰል ውጤት እንዲተጋ ማነቃቂያ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በ2017 በጀት ዓመት የህዝብ የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እንዲሁም ነዋሪውን ህብረተሰብ ከአስተዳደሩ ጋር በማገናኘት ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዕውቅና አሰጣጥ መርሐ-ግብሩ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።
በታምራት ቢሻው