በየመን ባህር በትናንትናው ዕለት 150 ሰዎችን ያሳፈረች ጀልባ ባጋጠማት ከባድ የአየር ሁኔታ መስጠሟን ተከትሎ ከ60 በላይ ፍልሰተኞች ህይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
ጀልባዋ በየመን ደቡባዊ ክፍል አቢያን በተባለ አካባቢ የሰጠመች ሲሆን፣ እስከ አሁን 68 አስከሬኖች መገኘታቸውን የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ኃላፊ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
12 ሰዎች በህይወት እንደተረፉ እና በርካቶች የደረሱበት አለመታወቁን ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አደጋውን ልብ ሰባሪ ሲል የገለጸው አይ ኦ ኤም፣ በአደጋው ሰለባ ከሆኑ ተጓዦች መካከል አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ እንዳልቀረም ጠቅሷል፡፡
የመን ከአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወደ አረብ ባህረሰላጤ ሀገራት ለሥራ ፍለጋ የሚሄዱ ፍልሰተኞች ዋነኛ መተላለፊያ ሆናለች ሲልም አይ ኦ ኤም ገልጿል፡፡
በዚህም በጀልባ መስጠም አደጋ በቅርብ ወራት ውስጥ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ማለፉን አሊያም መጥፋታቸውን ድርጅቱ አያይዞ ጠቅሷል፡፡
የአይ ኦ ኤም የየመን ዋና አዛዥ አብዱሳተር ኢሶቭ፣ ጀልባዋ በሰፊው የባሕር ዳርቻ ላይ ወደ 157 የሚጠጉ ስደተኞችን አደገኛ በሆነ መንገድ እያጓጓዘች እንደነበር ገልጸዋል።
ይህም አብዛኛውን ጊዜ በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በታምራት ቢሻዉ