የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው ዘርፈ ብዙ ትሩፋት የሚያስገኝ ተግባር መሆኑ ተገለፀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት በድሬዳዋ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን በማኖር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስጀመሩ ሲሆን፤ የልማት ስራዎች እንቅስቃሴንም ጎብኝተዋል።
ላለፉት ሶስት ቀናት ሲከናወን በቆየው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ አመራሮች እና አምባሳደሮች ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያውያንን በፍቅር እና በአንድነት ለሀገር ከፍታ በጋራ እንዲቆሙ ያስቻለ ድንቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ተፅዕኖን በመቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞን እያፋጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ የብልጽግና ጉዞ ማስተሳሰሪያና ማሳኪያ የሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮጀክት በስኬት እየተጓዘ ይገኛልም ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገራችን በአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮጀክት እያከናወነች የምትገኘው አብነታዊ ተግባር ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ብልፅግና መሳካት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ ተናግረዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ መትከል ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ፍቅርን፣ ሰላምንና አንድነትን ከመላው የቀጣናውና የአፍሪካ ሀገራት ጋር የሚገነባበት አስተሳሳሪ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የሚተከሉት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በጥንቃቄ ተንከባክቦ ማሳደግ የሁላችንም ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ፤ በድሬዳዋ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአመራሮችና በነዋሪዎች ውብ ቅንጅት እየተመዘገበ የሚገኘውን ውጤት በዘላቂነት ለማስቀጠል የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ፕሮጀክት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።