የልብ ህመም በተለያየ መንገድ እንደሚመጣ የሚናገሩት የኸርት አታክ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅና የውስጥ ደዌ ሀኪም ዶክተር ኦፕስኔት መርዕድ፣ በዋነኛነት በደም ግፊት አማካኝነት እንደሚከሰት ይገልፃሉ፡፡
ደምግ ግፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ የጤና እክል ነው ያሉት ዶክተር ኦፕሲኔት፣ በአፍሪካ 50 በመቶ የሚሆነው ማህበረሰብ የዚህ ችግር ተጠቂ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ችግሩ እንዳለባቸው የሚያውቁት 27 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥም ደግሞ መድሃኒት የሚወስዱት 18 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡
ሌላው ለድንገተኛ የልብ ህመም መንስዔ የሚሆኑት ኮሌስትሮል፣ ስኳር አብዝቶ መጠቀም፣ ጮማ ስጋ ማብዛት፣ ነጭ ዳቦ፣ ፓስታ አብዝቶ መጠቀም እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ድንገተኛ የልብ ህመምን ለመከላከልና ህይወትን ለማዳን፣ ወቅቱን የጠበቀ ቅድመ ጤና ምርመራ መለመድ እንዳለበት ዶክተር ኦፕሲኔት ይመክራሉ።
በኢትዮጵያ ለመከላከል ሳይሆን ለመታከም ወደ ጤና ተቋማት መሄድ የተለመደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሰለጠነው ዓለም ቅድመ መከላከል ላይ በትኩረት እንሚሰራ አስረድተዋል።
ቅድመ- ጤና ምርመራ፣ ተጓዳኝ ህመሞችን በወቅቱ መታከም፣ አትክልትና ፍራፍሬን መመገብ እንዲሁም ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ትኩረት መስጠት ድንገተኛ የልብ ህመምን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን አስምረውበታል።
በአለኸኝ አዘነ