በ2017 በጀት ዓመት ከ230 ሺ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመረከብ ለመስጂድ፣ ለመድረሣና ለመቃበር አገልግሎት ልማት ማዋሉን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታውቋል።
ምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት፣ 3ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ፣ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ምክር ቤቱ ባለፈው አንድ አመት ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ የሚያነሳቸውን ማህበራዊ፣ ሀይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር የተደረገው ትብብር በርካታ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ለዚህም አስተዳደሩን አመስግነዋል።
በተለይ በ2017 በጀት ዓመት ከ60 ሺ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ለመስጂድ እና ለመድረሣ፣ 170 ሺ ካሬ ሜትር መሬት ደግሞ ለመቃበር አገልግሎት የሚውል በመረከብ ለልማት እንዲውሉ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
ማህበራዊ ሀላፊነትን ከመወጣት አንጻርም፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በክልል ከተሞች ጭምር የገቢ መጠናቸው ዝቅተኛ ለሆኑና በተለያዩ ሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማእድ በማጋራትና የቤት ዕድሳት በማድረግ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ መደረጉንም በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ በሀገራዊ ጉዳይ ላይም በተለይ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎ፣ በሀገራዊ ምክክርና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ህዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን የጠቆሙት ሼህ ሱልጣን፣ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
እንደ ሀገር እየተከናወነ ያለው የመጅሊስ ምርጫ የተሣካ እንዲሆን እንደ ምክር ቤት እያገዝን እንገኛለን ያሉት ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን፣ መላው ሕዝብ በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ላይ የነቃ ተሣትፎ እንዲያደረግ ጥሪ አቀርበዋል።
በአንዋር አህመድ