ኢትዮጵያ በምታሰናዳው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ አዲስ አበባን ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነዉ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በምታሰናዳው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ አዲስ አበባን ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነዉ

AMN ሃምሌ 30/2017

ኢትዮጵያ በምታሰናዳው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ አዲስ አበባን ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ ተሳታፊዎች መዋለ ንዋያቸውን በዘርፉ ፈሰስ እንዲያደርጉ ለማስቻል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በመዲናዋ የተከናወኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ተሞክሮን በመቀመር በቀጣይ ለሚካሄዱ መሰል ሁነቶች ያሉ የቱሪዝም አቅሞችን ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ነዉ የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ያስታወቀዉ፡፡

አዲስ አበባን የኮንፍራንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከል ለማድረግ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች በርካታ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል።

ከተማዋን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን እውን እያደረ ከመገኘቱም ባሻገር ዘርፉን በአግባቡ ሊመራ የሚችል ተቋምን እውን አድርጓል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ራሱን ችሎ መቋቋሙ ከተማዋን ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የነበረውን ክፍተት በመሙላት ከተማዋ በቱሪዝም ዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም በመሸጥ ለሀገር እድገት ሚናውን በሚገባ እንዲወጣ ያስችላል ሲሉ ያብራራሉ።

ኢኮኖሚው ብዝሀ ዘርፍ እንዲሆን መንግስት ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ማግኘት መቻሉን፣ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣የአድዋ ሙዚየም ፣የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

መሠል መሠረተ ልማቶች ለቱሪዝም ኮንፈረንስ ፍሰት መጨመር አመላካች ከመሆኑም በላይ ከተማዋ ራሷን በአዲስ ውበት እንድትገለጥ አስችሏል።

በመዲናዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ150 በላይ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶች መካሄዳቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በመዲናዋ በርካታ ተሳታፊዎች የሚታደሙበትን ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ከተማዋን በሚመጥን ደረጃ ለዓለም ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም የጉባኤው ተሳታፊዎች በቆይታቸው ኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነትን ባሳየ መልኩ መልካም መስተንግዶና ገፅታን ይዘው እንዲሄዱ ብሎም የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስጎብኘት ቆይታቸውን እንዲያራዝሙና በከተማዋ የቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review